በምዕራብ ጎንደር ዞን የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርብ ቀን ለመመለስ እየተሠራ ነው።

18
በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሐምሌ 29/2018 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው የኤሌክትሪክ ኀይል መቋረጥ የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ በማስተጓጎል በሕይወታቸው እና በአካባቢው ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና አሳድሮ ቀይቷል። በግል እና በመንግሥት ተቋማት ላይ አሉታዊ ጫና እያደረሰ ይገኛል።
በገንዳ ውኃ ከተማ የሚገኘው የመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል የዚህ ችግር አንዱ ማሳያ ነው። የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይቋረጥ እንጅ ሆስፒታሉ ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታ በመጠቀም የ24 ሰዓት የሕክምና አገልግሎት እየሠጠ መኾኑን የሆስፒታሉ ተወካይ ኀላፊ ይስማው በጎሰው ይናገራሉ።
አሁን ላይ መብራት ባለመኖሩ የተቋሙን የውስጥ ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለነዳጅ ፍጆታ እየዋለ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ሆስፒታሉ በቀን ከ57 ሺህ ብር በላይ ለነዳጅ ፍጆታ ወጭ እንደሚያወጣ የተናገሩት ተወካይ ኀላፊው በዞኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ ጀምሮ እስካሁን ከአራት ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ያላነሰ ወጭ ማውጣቱን አረጋግጠዋል።
ይህ መኾኑ ደግሞ በቂ እና አስፈላጊ የሕክምና ግብዓት ለማሟላት እንቅፋት መፍጠሩንም ነው አቶ ይስማው በጎሰው የገለጹት። መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በየጊዜው የሚፈጠረውን የኀይል መቆራረጥ በዘላቂነት ሊፈታው ይገባልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ትራንሰሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ጌታቸው ተሻገር ከአዘዞ መተማ በተዘረጉ 19 ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኀይል ተሸካሚ ምሰሶዎች (ታወሮች) ላይ በተፈጸመ የዘረፋ ወንጀል ምክንያት ታወሮቹ በንፋስ መውደቃቸውን አንስተዋል።
በዚህ አደጋ ሳቢያ በቋራ፣ መተማ፣ አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳዎች፣ በገንዳ ውኃ እና መተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።
የተበላሹ እና የወደቁ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በመጠገን እና በማቆም የኀይል አቅርቦቱን ዳግም ለማስጀመር ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷልም ነው ያሉት።
የጥገና ሥራው ተጠናቅቆ መስከረም ወር መጨረሻ ላይ አገልግሎት ለመስጠት ቢታቀድም በወሩ መጨረሻ ተጨማሪ ሁለት ታወሮች በስርቆት ምክንያት በመውደቃቸው በታቀደው ጊዜ አገልግሎቱን መመለስ እንዳልተቻለ ነው የገለጹት።
አሁን ላይ ከወደቁት 19 ታወሮች መካከል የ16ቱ ጥገና ተጠናቅቋል፤ ቀሪ ሦስት ታወሮችን ለማቆም ጥረት እየተደረገም ነው፤ የገመድ (የኮንዳክተር) ዝርጋታ ሥራም እየተከናወነ ነው።
የታወር ጥገናውን በአሥር ቀን ውስጥ ለማጠናቀቅ እና አገልግሎቱን ለመመለስ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው ተሻገር የጥገና ሥራው በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የዞኑ ማኅበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
የኀይል አቅርቦቱ የመጀመሪያ ተጠቃሚውም ኾነ ተጎጂው ሕዝቡ በመኾኑ ማኅበረሰቡ የመብራት መሠረተ ልማቶችን “የኔ ነው” በሚል ስሜት ሊጠብቅ እና ዝርፊያ የሚፈጽሙ ወንጀለኝችን መከታተል እና አጋልጦ መሰጠት እንደሚገባም ተመላክተዋል።
✍️ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleእሳቱን የቀመሱት ኀይሉን ያውቁታል።
Next articleየባሕር በር እጦት በየሦስት ዓመቱ አንድ የሕዳሴ ግድብ የሚያሰገነባ ሃብት እንደሚያሳጣ ያውቃሉ ?