
“የኢትዮጵያን ወታደር ማን ያውቀዋል ቢሉ የቀመሰው” በሚል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሠራዊቱን ጽናት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ከዘመናት ፈተናዎች ማዶ ድልን ተጎናጽፎ የመውጣት ምስጢሩን ያብራራሉ።
በወታደራዊ ሳይንስ ብቻ ስለ ኢትዮጵያ ሠራዊት ማውራት ፈጽሞ አይቻልም፤ ማንነቱ የሚለካው እንደ ዓድዋ፣ ጉራዕ እና ጉንደት ባሉ ዐውደ ውጊያዎች በተግባር ሜዳ ላይ እንጂ በወረቀት ላይ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከሩ ኀይሎችም የሠራዊቱን ክንድ በመቅመስ ጽናቱን በአደባባይ ተረድተውታል።
ዛሬም ይህ የያኔ ታሪካዊ እውነት ሠራዊቱ በምድር እና በአየር በቃኘው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም እና በሚወስዳቸው መራራ እርምጃዎች ዳግም አረጋግጧል።
ሀገሪቱ የገነባችው ይህ የማይናወጥ ጽናት “ኢትዮጵያን አይችሏትም” የሚለውን እውነት ያስመሰክራል። የሚገኘውም ድል የአፍሪካን የነጻነት እናትነት ዳግም የሚያረጋግጥ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ራሱ በድል ማኅፀን የተገነባ በመኾኑ ሠራዊቱ ከማሸነፍ ውጪ ሌላ አማራጭ አያውቅም፤ መንፈሱም ለሀገር ክብር በቆረጠ ጽኑ ሐቅ ላይ ጸንቶ ዘልቋል።
እሳቱን የቀመሰው አካል ብቻ ኀይሉን እንደሚያውቀው ሁሉ ዛሬ ያሉት ጀግኖችም ጠላቶች የሠራዊቱን ልክ እንዲያውቁ በማድረግ ታሪካዊ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኔ ከእናንተ መካከል የወጣሁ እና በእናንተ መካከል የምኖር በመኾኔ ድርብ ኩራት ይሰማኛል” እንዳሉት መላው ሕዝብ በሠራዊቱ ላይ የላቀ ኩራት ይሰማዋል። የኢትዮጵያ ወታደር እና ኢትዮጵያዊነት የጋራ ዕጣ ፈንታ ባለቤቶች በመኾናቸውም ሠራዊቱ ሁሌም የማይበገር እና ለድል የታጨ የሉዓላዊነት ጠባቂ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመቻ አካሂዶ የመጨረሻውን ድል በማስመዝገብ ረገድ የሠራዊቱ ምሁራን ኀይሎች ሚና ከፍተኛ መኾኑ ለጀግንነቱ ማረጋገጫ አድርገዋል።
የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በበኩላቸው መከላከያ ሠራዊቱ የከዳተኞችን እና የባንዳ ሴራዎችን እያከሸፈ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የሀገርን የከፍታ ጉዞ በድል ማማ ላይ በማጽናት ታሪካዊ አደራውን እየተወጣ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
