
“ነጩ ወርቅ” እየተባለ የሚጠራው ሰሊጥ ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንዱ ነው። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2018/19 የምርት ዘመን የተሻለ የሰሊጥ ምርት በማምረት ኢኮኖሚውን ለመገንባት እየተሠራ ይገኛል።
የጃዊ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበራ ባዘዘው በ2018/19 የምርት ዘመን በወረዳው ሰፊ የኾነ የአኩሪ አተር እና የሰሊጥ ምርት እንደሚመረት ገልጸዋል። በተለይም የሰሊጥ ምርት በወረዳው በስፋት የሚታወቅ ነው። በምርት ዘመኑም 18 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰሊጥ ሰብል መሸፈኑን አንስተዋል። የሰሊጥ ሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ባለፈ የአረም እና ኩትኳቶ ቁጥጥር ሥራ በወቅቱ መሠራቱን ነው ያስታወሱት። አሁናዊ የሰብል ቁመናውም መልካም እንደኾነ ተናግረዋል። ምርቱ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት እና የምርት ብክነት እንዳይከሰት የአርሶ አደሮችን አደረጃጀት በመጠቀም በቅንጅት የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በወረዳው እስካሁን 115 ሄክታር መሬት የሰሊጥ ምርት ተሰብስቧል። ምርቱን በወቅቱ ለመሰብሰብም በርካታ የቀን ሠራተኞች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ቤዛዊት ጌታሁን በ2018/19 የምርት ዘመን በዞኑ 19 ሺህ 655 ሄክታር መሬት በሰሊጥ በመሸፈን ከ155 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።የታቀደው ምርት እንዲሳካ ግብዓት በወቅቱ ከማሠራጨት ባለፈ በቅርበት ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። የሰብሉ ቁመና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ምርቱም እየተሰበሰበ መኾኑን ገልጸዋል።ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 303 ሄክታር መሬት የሰሊጥ ሰብል መሰብሰቡን ያስረዱት ኀላፊዋ የምርት ብክነት እንዳይከሰት የሰው ኃይል በመጨመር የመሰብሰብ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። የሚጠበቀው ምርትም እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
