
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አዲሱን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ፕሮጄክት ግንባታ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ቤተ መንግሥቱን ለመገንባት ቀደም ብሎ ዕቅድ ተይዞ እንደነበር ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ የክልሉ መንግሥት ጽሕፈት ቤት ኾነው የቆዩ ሕንጻዎች ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ፣ ሰፊ አገልግሎት የሰጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
እስካሁን የነበሩት ሕንጻዎች አገልግሎታቸውን ጨርሰዋል፤ ነገር ግን ጠብቀን ለትውልድ እናስተላልፋቸዋለን ነው ያሉት። ታሪክን መጠበቅ እና ማደስ የመንግሥት ትኩረት መኾኑንም ገልጸዋል።
በዚህ ዘመን የሕዝባችንን ታሪክ፣ ባሕል እና እሴት የሚገልጽ ቤተ መንግሥት መገንባት አስፈልጓል ብለዋል። በዚህ ዘመን ያለን መሪዎች ለቀጣይ ትውልድ አሻራ ማስቀመጥ አለብንም ነው ያሉት። ዛሬ ያስጀመርነው ሥራ ሃሳባችን በቁስ እና በቅርስ መልክ ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፍበት አሻራ ነውም ብለዋል።
ሥራው የክልሉ ሕዝብ ወካይ እና ምልክት መኾኑንም አንስተዋል። የክልሉን ሕዝብ እና ታሪክ የሚመጥን ፕሮጄክት እንደኾነም ገልጸዋል። ባለፉት ጊዜያት ፕሮጄክቱን ለማስጀመር የሚያስችል ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።
ይህ የክልላችን ሕዝብ ምልክት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሀገራት የሚገለጹበት እና ምልክት የሚያደርጉት ሥራ አላቸው፤ ዛሬ የተጀመረው ፕሮጄክት የክልላችን ምልክት ነው፣ ተራ ፕሮጄክት አይደለም፣ ትልቅ አሻራ እና ምልክት ነው ብለዋል።
በዓባይ እና በጣና ዳርቻ የሚገነባውን ፕሮጄክት ታሪክን በጠበቀ መልኩ በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግሥት ሥራው በጥራት እና በፍጥነት እንዲገነባ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
