“ዛሬ የተጀመረው ፕሮጄክት ዘመን የሚሻገር፤ የአማራ ክልልን ሕዝብ ባሕልና ታሪክም የሚገልጽ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

10
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አዲሱን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ፕሮጄክት ግንባታ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ብልጽግና ፓርቲ መሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይኾን ሥራን በአጭር ጊዜ ጨርሶ ያሳያል ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል። ባሕር ዳር ባለብዙ ታሪክ ከተማ ናት ብለዋል። ዓባይ እና ጣና ያስዋቧት ከተማ መኾኗንም ገልጸዋል።
ፕሮጄክቱን ለመጀመር በርካታ ጊዜ ተሞክሮ እንደነበር የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገቢው መንገድ ተጠንቶ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። ጣና እና ዓባይን ያማከለ ትልቅ ቅርስ መኾኑንም አንስተዋል።
የክልሉ መንግሥት የሥራ ማከናወኛ ብቻ ሳይኾን ሌሎች የሕዝብ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል፣ ታሪክ እና ባሕል የሚገለጽበት መኾኑን ነው የተናገሩት።
እንደ ኢትዮጵያ ትልቅ ጸጋ የተሰጠው ሀገር ያለው የለም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ግን ሀገርን ሃብታም እንደማያደርግ ገልጸዋል። የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ጸጋዎች አልምቶ ለትውልድ የማስተላለፍ ርዕይ ይዞ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ለትውልድ የሚተርፍ ወረት ካልተላለፈ የሀገር ቀጣይነት እና የትውልድ ቀጣይነት አይኖርም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ እጅግ ሉዓላዊ የኾነች፣ ዳር ድንበሯን የምታስከብር፣ የባሕር በሯን ለማስመለስ የምትሠራ፣ ለአፍሪካ ምሳሌ የምትኾን ናት ብለዋል። የትኛውም ችግር ቢመጣ ተቋቁማ የምታልፍ እና ማንም ተጽዕኖ የማያደርግባት ሀገርን የመገንባት ዓላማ ይዘን እየሠራን ነው ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው ፕሮጄክት ዘመን የሚሻገር፤ የአማራ ክልልን ሕዝብ ባሕል፣ ታሪክ እና ሃይማኖት የሚገልጽ ያማረ እንደኾነ ነው የተናገሩት። ባሕር ዳር በብዙ መልኩ እየተለወጠች ነው፣ ነገር ግን ይህ የባሕር ዳር ጸጋ ገና አልታወቀም፣ ገናም ባለው ልክ አልተገለጠም ነው ያሉት።
የከተማዋን ጸጋ በአግባቡ መለየት እና ማልማት እንደሚገባ አመላክተዋል። ጠንካራ መንግሥት የሚኖረው ውጤታማ ሥራዎች ሢሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል። የሃሳብ ሃብት ካለ ትልልቅ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ዛሬ የተጀመረው ሥራ የክልሉን ሕዝብ ማክበር ነው፤ ተገልጋዩን ማክበር ነው፤ ትልቅ ሥራም ነው ብለዋል።
✍️ ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ባሕር ዳር የከተማ ውበትን ከመደመር መንግሥት የሥልጣኔ ግብ ጋር አስተሳስራ የዘመናዊት ኢትዮጵያን አዲስ ገጽታ እያንፀባረቀች ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next article“ዛሬ የተጀመረው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ፕሮጄክት የክልላችን ምልክት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ