
በኢትዮጵያ የመከላከያ እና ብሔራዊ ደኅንነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ገናና የባሕር ኃይል እንደነበራት በርካታ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። ሀገሪቱ በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ የንግድ መስመሮች ለዘመናት የተጫወተችው ሚና ይህንን የሚያስረዳ ነው።
በወቅቱም በአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ የባሕር ኃይሎች መካከል አንዱ ነበር። ነገር ግን በቀደሙት የሥርዓት ለውጦች በተፈጠረው የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ የባሕር በሯን እንድታጣ፤ የባሕር ኃይሏም እንዲበተን ተደርጓል።
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን የቀደመ ገናናነቷን ለመመለስ፣ የባሕር በር ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የባሕር ኃይሏን በመገንባት ላይ ትገኛለች። የባሕር ኃይሉ እንደገና ተቋቁሟል። ለዋና መሥሪያ ቤቱ ዘመናዊ ሕንጻ ተገንብቷል። የሥልጠና ማዕከል ተደራጅቶ ብቁ ባሕረኞችን በማፍራት ላይ ይገኛል።
ዓላማውንም ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ የቀይ ባሕር ባለቤትነት መመለስን አድርጓል። ይህንን የቁጭት ዓላማ የያዘው ተቋምም ባለተስፋዎችን በንድፈ ሀሳብ፣ በተግባር እና በውኃ ላይ ሥልጠናዎችን በሚገባ እያሠለጠነ ነገ ለሚጠብቀው ሀገራዊ ግዳጅ እያዘጋጃቸው ይገኛል።
በዚህም የትናንት ታሪክን በቁጭት እያስታወሱ፣ ዛሬ ላይ እየተዘጋጁ፣ ነገን አሻግረው በጉጉት የሚጠብቅ ባሕረኞች እየተፈጠሩ ነው። ባሕር ኃይሉም በሥልጠና እየተገነባ የሰው ኃይል፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ እየታጠቀ የተቋም ግንባታ ሂደቱ ቀጥሏል።
ቀጣይ የኢትዮጵያን መሻት ዕውን የሚያደርግ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብር፣ ማንኛውንም የውኃ ላይ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችል የባሕር ኃይል በአቅም እየጎለበተ ይገኛል።
በእስካሁኑ ጉዞው ብቁ ባሕረኞችን አሠልጥኖ በማስመረቅ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ደኅንነት 24 ሰዓት የመጠበቅ ግዳጅን በተግባር መወጣት ጀምሯል። ለኢትዮጵያ የንግድ መሠረት የኾኑትን መርከቦችን ከመነሻ እስከ መዳረሻቸው የ24 ሰዓት ክትትል ያደርጋል። ለዋናው የቀይ ባሕር ግዳጅም እየተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ እንደተናገሩት ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይልን ማጠናከር የምርጫ ጉዳይ ሳይኾን ግዴታ ነው ብለዋል። የባሕር ኃይሉ ተልዕኮ በሀገር ውስጥ የውኃ አካላት ደኅንነትን በመጠበቅ በዓለም ዓቀፍ የውኃ ቀጣናዎች ላይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው ብለዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያን የሚመጥን፣ ወደ ቀደመ ገናናነቷ የሚመልስ፣ በቀይ ባሕር ቀጣና የሚቃጡ ጥቃቶችን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል የባሕር ኃይል እየተገነባ እንደሚገኝም ዋና አዛዡ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
