
“አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ መልዕክት 12ኛው የጣና ከፍተኛ ደረጃ የመሪዎች ፎረም በባሕር ዳር ከተማ ጣና ዳርቻ ላይ ይካሄዳል።
ባለፉት 11 ዓመታት ውስጥ በአሕጉራዊ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ባሕር ዳርን መገናኛው ያደረገው ፎረሙ የአፍሪካ ልሂቃን የሚመክሩበት ማዕከል ኾኖ ዘልቋል።
ጣና ፎረም የአፍሪካን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ መሠረታዊ የፖሊሲ ሀሳቦች የሚመነጩበት የሀሳብ ማዕከልም ነው። አፍሪካ ከውጭ የሚመጡ ጫናዎችን ተቋቁማ የራሷን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የምትችለው የውስጥ ሰላሟን እና ጸጥታዋን ስትቆጣጠር ነው።
የጣና ዳርቻዋ ባሕር ዳር ይህንን አሕጉራዊ አጀንዳ ስትቀበል ለአፍሪካ የሰላም ፍለጋ ያላት አቋም የማይናወጥ መኾኑን በገሀድ ታሳያለች። ይህም ፎረሙ አሕጉራዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሔዎች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ማዕከላዊ ሚና መጫወቱን ቀጥሏል።
12ኛው የጣና ፎረም የአፍሪካን የሰላም አቅጣጫዎች ከማመላከት ባለፈ የኢትዮጵያን የኮንፈረንስ ቱሪዝም አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ታላቅ ድል ነው።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የጣና ፎረምን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ መድረኩ የዲፕሎማሲ መድረክ ብቻ ሳይኾኑ የሀገርን ገጽታ እና የኢኮኖሚ አቅም ከፍ የሚያደርጉ የድል አውድማዎች መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ከተለያዩ የአፍሪካ ማዕዘናት እና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ እንግዶች የባሕር ዳርን የተፈጥሮ ጸጋ፣ የታሪክ ቅርሶች እና የሰዎች ፍቅር ቀርበው ሲያዩት የኢትዮጵያ የቱሪዝም አምባ የማይናወጥ መኾኑን ይገነዘባሉ።
መንግሥት ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ እና ክልሉ እንዲመጡ የሚሠራቸው የማስተዋወቅ ሥራዎች ከፍ ወዳለ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል። እንደዚህ ያሉ ፎረሞች ጎብኝዎች የክልሉን የቱሪዝም መስህቦች በአካል ተገኝተው እንዲጎበኙ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥሩም አቶ ዓባይ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች የፎረሙን ስኬት እና የከተማዋን ውበት በአካል ተመልክተው ወደ ሀገሪቱ እና ክልሉ ዳግም ለመምጣት የጉዞ ዕቅዳቸውን እንዲያስተካክሉ አስተማማኝ መሠረት ይጥላል።
በአጠቃላይ እንደ ባሕር ዳር ያሉ ከተሞች ዓለም አቀፍ መሪዎችን፣ ተመራማሪዎችን እና ባለሙያዎችን በብዛት ሲያስተናግዱ የሆቴል፣ የትራንስፖርት፣ የዕደ ጥበብ እና የዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፎች የጥራት እና የብቃት ከፍታቸውን እንዲጨምሩ ያስችላል።
እንዲህ አይነት ፎረሞች ከቱሪዝም ዕድገት ጋር ተደጋግፈው ሲጓዙ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ እና በዲፕሎማሲ ያላት ተሰሚነት ዘላቂ መሠረት ይይዛል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
