አፍሪካ ቀንድ ጋሻ፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከታ

13
‎ድንጋይ ተንተርሰው፣ ፀሐይ፣ ብርድ፣ ቁር፣ ነፋስ እና ዝናብ ሳይበግራቸው ሀገር አጽንተው የኖሩት የጀግኖች አባቶች የአርበኝነት ታሪክ ዛሬም በልጆቻቸው እጅ በዘመናዊ መንገድ ቀጥሏል።
ከጥንት ጀምሮ በደማቸው የተሠራችው ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯን እና ሉዓላዊነቷን አስከብራ የዘለቀች ሲኾን፣ ዛሬ ላይ በቀጣናው እና በአፍሪካ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል እየገነባች ትገኛለች። ‎በዚህ ሀገራዊ ግንባታ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአፍሪካ ቀንድ እና በምሥራቅ አፍሪካ አስተማማኝ የአየር የበላይነትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ታሪካዊ ተቋም ነው።
ተቋሙ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባለፈ በቀጣናው ያለውን ኃይል በመጠበቅ እና ሰላም በማስከበር ረገድ የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል።
‎​
‎በሀገሪቱ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እና የትጥቅ ግንባታ ላይ የሚገኘው አየር ኃይሉ፤ የላቁ ተዋጊ ጀቶችን እና ዘመናዊ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችሉ የውጊያ አውሮፕላኖችን በመታጠቅ የአየር ክልሉን በበላይነት የመጠበቅ አቅሙን አሳድጓል። ዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂን በተለይም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ አዳዲስ አቅሞችን በመጨመር ላይ ይገኛል።
‎
‎በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበቃ እና የታጠቀ የሰው ኃይል መገንባት ተችሏል። ዘመናዊ የአየር ክትትል፣ የራዳር ሥርዓቶች፣ የአየር መከላከያ አቅሞችን እና የአውሮፕላን ጥገና አቅሙን አሳድጓል። የሀገሪቱን የአየር ክልል አይደፈሬ ማድረግ ችሏል። በተለይም የዘመናት የተግባር ውጊያ እና የስትራቴጂክ አመራር ልምድ ተቋሙን ልዩ ብቃት አጎናጽፎታል። ለቀጣናውም አስተማማኝ የሰማይ ኃይል ገንብቷል።
‎
‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት ዓመታት ካስመዘገበው ታሪካዊ ውጤት በላይ በአሁኑ ወቅት የላቀ የሰው ኃይል እና የዘመነ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ በቀጣናው ጠንካራ ዘመናዊ ወታደራዊ አቅም መገንባቱን ገልጸዋል። አየር ኃይሉ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ከመጠበቅ ባለፈ፤ ሀገራዊ አቅምን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ድሮኖችን በሀገር ውስጥ በማምረት የመሰለል እና ጥቃቶችን የመሰንዘር ከፍተኛ ብቃት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
‎
‎ይህም ለአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እና ለአፍሪካውያን ትልቅ ኩራት መኾኑን ነው ያስረዱት። በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር የአየር የበላይነቷን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ ብቃት መታጠቋን ነው የገለጹት። በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍ ኃያልነቷን ታስቀጥላለች ብለዋል።
‎
‎ሀገሪቱ የገነባችው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም ቀጣናው ከሽብርተኝነት ስጋት ለመጠበቅ እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው። ይህ የተገነባው ዘመናዊ እና ስትራቴጂካዊ የጦር አቅም የኢትዮጵያን ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር፣ ለምሥራቅ አፍሪካ እና ለአሕጉሩ ሰላም እና ብልጽግና አለኝታ እና ጋሻ የሚኾን አስተማማኝ ተቋም ተገንብቷል ነው ያሉት።
‎
‎
‎
‎ዘጋቢ:-ሥራውድንቅ ደሳለው
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከካይሮ እስከ አሥመራ የተሸረበው ሴራ እና የኢትዮጵያ የባሕር በር እውነት።
Next article12ኛው የጣና ፎረም ከጥቅምት 13 /2019 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ይካሄዳል።