
ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔዋ መነሻ፣ የታሪካዊ ክብር እና የኢኮኖሚ ጥንካሬዋ መሠረት እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት ሀገሪቱ ይህንን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብቷን አጥታ የባሕር በር አልባ ለመኾን ተገድዳለች።
ይህ ሁኔታ በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይኾን በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በነበሩ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፣ በውጭ ኀይሎች እኩይ ሴራ እና በወቅቱ በነበሩ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ መሪዎች ደካማ ውሳኔ የተፈጠረ የታሪክ ስህተት ነው።
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የባሕር በሯን እንድታጣ ከተደረገባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል በካይሮ እና በሻቢያ ለዘመናት የተጠነሰሰው እኩይ ሴራ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሰለሞን ተፈራ እና የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው ያዕቆብ ኃይለማሪያም (ዶ.ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ የተደረገበት ዋነኛው ምክንያት ሀገሪቱ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ለማዳከም እና በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ጠንካራ የጂኦ-ፖለቲካዊ የበላይነትን ለማክሸፍ ታስቦ የተሠራ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ እንድትኾን የተደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ የተወያየበት እና የወሰነበት ሀገራዊ ውሳኔ ሳይኾን በወቅቱ በነበሩ የሀገር ውስጥ እንደራሴዎች እና ባለሥልጣናት በተወሰነ ደካማ የፖለቲካ ውሳኔ ነው።
በዚህ አሳዛኝ ታሪካዊ ስህተት ምክንያት ኢትዮጵያ ላለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት ከፍተኛ የጂኦ-ፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ውስጥ እንድትወድቅ እና ለወደብ አገልግሎት ከፍተኛ ወጪ እንድታወጣ ተገድዳ ቆይታለች።
ታዲያ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ስህተት ለማስተካከል እና በቀጣናው ላይ ዘላቂ ሰላም እና የጋራ ዕድገት ለማምጣት አዲስ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት በተፈጥሮ ፍላጎት ሳይኾን በወቅቱ መሪዎች ስህተት እና በውጭ ጫና የተከሰተ ሀገራዊ ጉዳት ነው።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ዘመናዊ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊኾን እንደማይችል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ የባሕር በር ተጋሪነቷን ለማረጋገጥ የያዘችው አቋም በኀይል ሳይኾን ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና “በሰጥቶ መቀበል” መርህ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።
የግዙፍ ቁጥር ሕዝብ ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ካላገኘች በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እና የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር እንደማይችል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መረዳት ጀምሯል።
ተፈጥሯዊ የባሕር በር መብት ለማስከበር የሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያን የሕልውና እና የዕድገት መስመር የሚወስን ነው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
