12ኛው የጣና ፎረም ከጥቅምት 13 /2019 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ይካሄዳል።

10
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የጣና ከፍተኛ መሪዎች ፎረምን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢሮ ኀላፊው እንደገለጹት 12ኛው የጣና ከፍተኛ የመሪዎች ፎረም ከጥቅምት 13/2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም ድረስ በባሕር ዳር ይካሄዳል። ለዚህም በሚመለከታቸው አካላት በኩል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። ፎረሙ በአፍሪካ ሰላም ጉዳይ ቁልፍ የፖሊሲ ሃሳቦች የሚመነጩበት እና መፍትሔዎች የሚቀርቡበት ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።
“አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና ቀጣናዊ የፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ መልዕክት ላይ የተመሠረተ መድረክ ስለመኾኑም አብራርተዋል። አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው የሚፈቱበት መድረክ ነውም ብለዋል።
በአፍሪካ የሰላም ግንባታ፣ ጸጥታ እና ልማት፣ በአህጉሪቷ ለሚስተዋሉ ግጭቶች አፍረካዊ መፍትሔዎችን መሥጠት ላይ አጀንዳ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
በመድረኩ የአፍሪካ መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበራት አባላት፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና ሌሎችም የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ጣና ፎረም ባሕር ዳር ከተማ አሕጉራዊ ትላልቅ ኹነቶችንም በብቃት ማዘጋጀት እና መወጣት እንደምትችል ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ የምናሳይበት ነውም ብለዋል። ለዓለም አቀፍ ጎብኝዎችም የማኅበረሰቡን እንግዳ ተቀባይነት እና እሴት፣ የአካባቢውን የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ጸጋዎችን፣ የመስህብ ሀብቶቻችንን የምናስተዋውቅበት መድረክ ይኾናልም ነው ያሉት።
ፎረሙ የቱሪዝም ኮንፈረንስ አንዱ ክፍል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው ለዚህም የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በማቅረብ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኀን ሙያዊ እና ግልጽ አቅጣጫን በመከተል ሁነቱን ለሕዝብ የማድረስ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም፣ ልማት እና አንድነት ያላትን የማይናወጥ ሚና በግልጽ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር እና አካባቢው ሕዝብ የክልሉንም ኾነ የኢትዮጵያን እንግዳ ተቀባይነት በተግባር እንዲያረጋግጡም መልዕክት አስተላልፈዋል። ለፎረሙ ተሳታፊ አፍሪካውያን ወንድም እና እህቶች የሚጠበቅባቸውን የመስተንግዶ፣ የእንግዳ ተቀባይነትን እና ሰላምን በማረጋገጥ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአፍሪካ ቀንድ ጋሻ፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከታ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትን ጎበኙ።