
የሀገር ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ክብር የኢትዮጵያ የህልውና መሠረቶች ናቸው። በመኾኑም የትናንቱን አኩሪ እና ታሪካዊ ኢትዮጵያዊ አንድነት ዛሬም እንዳልደበዘዘ ማሳየት ተገቢ ነው።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ እና በቀይ ባሕር ተሳትፎዋ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች ነው። በዚህም በቀጣናው አጀንዳ ከመቀበል አልፋ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና አጀንዳ ሰጪ ሀገር ኾናለች።
ይህ ዓይነቱ የጠላት ሴራ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። የጣሊያን ወራሪ ሉዓላዊነታችንን ሊገፍ ሞክሮ ነበር። ያኔ አጼ ምኒልክ ታሪካዊ የክተት አዋጅ አወጁ። ይህ አዋጅ ዛሬም ለሚመጣ ጠላት የምንሰጠው የጋራ ምላሻችን ነው።
በአጼ ምኒልክ የተላለፈው የወቅቱ ሀገራዊ ጥሪ በወቅቱ የነበረውን ማንኛውንም የውስጥ የእርስ በእርስ ሽኩቻ በአንዲት ጀንበር አቅልጧል። ይህም ኢትዮጵያውያን የሀገር ኅልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው እንደ አንድ ሰው የሚነሱ መኾናቸውን ለዓለም አረጋግጧል።
የእቴጌ ጣይቱ የማይበገር የሀገር ፍቅር የዛሬው ትውልድ አርዓያ ነው። በውጫሌ ውል የጣሊያን ሸፍጥ ላይ ያሳዩት ቆራጥነት ታሪካዊ ነው። “ሀገሬን ከሚያሳንስ ውል ሞትን እመርጣለሁ!” በማለት የሀገርን ክብር አስቀድመዋል።
የጣይቱ ይኸው አቋም የሀገር ሉዓላዊነት በድርድር ሳይኾን ለሀገር ክብር ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ በመኾን እንደሚረጋገጥ ያስተምረናል።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እና ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ብቸኛው እና ትልቁ ድክመት የውስጥ ክፍፍል መኾኑን አሳይተዋል። ትልቁ ጥንካሬዋ ደግሞ የውጭ ጠላት ሲመጣ ያንኑ ክፍፍል ትታ የምትፈጥረው አልገዛም ባይነት መኾኑን አስገንዝበዋል።
የትላንቱን ታሪክ ከዛሬው ዘመን መፍትሔ ጋር በሚገባ አስተሳስረው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የትውልዱ ትልቁ መሣሪያ መተባበር መኾኑን ይገልጻሉ።
“አንድ ክር ደካማ ነው፤ ብዙ ክር ግን የማይበጠስ ገመድ ነው። ስንበዛ እና ስንሰናሰል በቀላሉ የማንበጠስ ጠንካራ ገመድ ስለኾንን መተባበርን፣ መከባበርን፣ በጋራ መቆምን፣ ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደምን ሀብት እና ስንቅ ማድረግ ይገባል” በማለት የጋራ ክንድን ወሳኝነት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነት ሲገልጹም “ኢትዮጵያን ኢትዮጵያዊ እያለ ማሸነፍ አይቻልም” ይላሉ።
ጠላት ኢትዮጵያን ለማዳከም በሚያደባበት በዚህ ወቅት የዓድዋ ጀግኖችን የደም ዋጋ በማሰብ ከውስጥ መከፋፈል ወጥቶ በአንድነት መቆም የህልውና ግዴታ ሊኾን ይገባል።
እንደ አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ጽናት ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ ሁሉንም ለሀገሬ በሚል ጽኑ መንፈስ በጋራ መሰለፍም ጊዜው የሚፈልገው ዋናው ጉዳይ ነው። የትኛውም ኀይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትም ኾነ የዕድገት ጉዞ ሊገታው እንደማይችልም በአንድነት ማሳየት ይገባል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#AMECO #Ethiopia #Sovereignty #AdwaSpirit
#ባሕር_ዳር #መስከረም_30_2019_ዓ_ም
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
