
ከንሥር በሚልቅ ፍጥነቱ ለጠላቶች ምትሀት ነው። በጥልቅ ምልከታው የጠላትን ዒላማ ነጥሎ ይመታል፤ ከዐይን ጥቅሻ የሚፈጥነው ጥቃቱ ጠላቶች ክብሯን ለመዳፈር እንዳያስቡ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ክብር ለዘመናት በጽናት ጠብቋል። በዚህም ጠላቶች የኢትዮጵያን ሰማይ ለመጣስ ቀርቶ ለማየት እንዳይደፍሩ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባሻገር የጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነት፤ የግዛት አንድነት እንዳይደፈር፤ ምሥራቅ አፍሪካ የአሸባሪዎች ቀጣና እንዳይኾን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተወጥታለች።
በየትኛውም የኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ግንባር ቀደም በመኾን የሀገርን ሉዓላዊነት እና ክብር በማስጠበቅ በኩል የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የዘመኑን የቴክኖሎጂ አብዮት የዋጀ፤ በዕውቀት እና በሥነ ምግባር የታነጸ፤ ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ የቆመ የደኅንነት ዋስትና ነው።
በአባላት ቁጥር ብቻ ያልተወሰነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ አየር ኀይል፤ በስትራቴጂክ መረጃ አቅም፤ በዘመናዊ የትጥቅ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ማፍለቅ ላይ የተመሠረተ ነው።
ተቋሙ ዘመናዊ የአየር ክትትል፤ የራዳር ሥርዓቶች፤ የአየር መከላከያ አቅሞች እና የአውሮፕላን ጥገና አቅሙን አሳድጓል። አየር ኀይሉ በቴክኖሎጂ፤ በሰው ኀይል ሥልጠና እና የዝግጁነት አቅምን በማሳደግ የሀገሪቱ የአየር ክልል አይደፈሬ አድርጓል።
ከትናንት እስከ ዛሬ በሰመረ የጸና አቋሙ፤ በከፍተኛ የውጊያ ብቃቱ እና በታሪካዊ የጀግንነት ገድሎቹ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ከውጭ ጠላቶች እና ስጋቶች በጽናት በመከላከል ታሪካዊ ክብሩን አስቀጥሏል።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር ጠንካራ የሰው ኀይል፤ ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ፤ ዘመኑን የሚመጥን መሠረተ ልማት ካለ ማንም ሀገርን ሊዳፈር አይችልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት አቅምን በመገንባት፤ የላቁ ተዋጊ አውሮፕላኖችን እና ሰው አልባ ድሮኖችን እና ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ጠንካራ የአየር ኀይል መገንባቷን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል ምክትል አዛዥ ለከባድ ጥገና ማዕከል ብርጋዴል ጄኔራል መሠረት ጌታቸው ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ጠንካራ ተግባራት የኢትዮጵያ አየር ኀይል አቅሙን እንዲያሳድግ፤ ቴክኖሎጂን እንዲታጠቅ፤ ቴክኖሎጂን እና የሀገር ሃብትን እንዲያለማ፤ ቴክኖሎጂን በላቀ ደረጃ እንዲተገብር አሥችሏል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል ለውጥ በተግባር የሚታይ፤ የሚዳሰስ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ አየር ኀይል ጋር ለመሥራት ጥረት ማድረጋቸውን ነው ያነሱት።
በተቋሙ ቴክኖሎጂን የማምረት፤ የመጠገን እና የመፈጸም አቅም አድጓል ብለዋል። ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ አቅም መፍጠር ተችሏል ብለዋል። ለብሔራዊ ጥቅም የሚመጥን አቅም ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የአየር ኀይሉ የመፈጸም አቅም እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያን ከመተንኮሳቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋልም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰሞኑ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ታላቅነት፤ የዓለም እና የአካባቢን ወቅታዊ ኹኔታ እንዲሁም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ኀይል እንዲኖረን እንሠራለን ነው ያሉት።
በቀጣናው የአየር ኀይል የበላይነትን ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ ትገነባለች ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
