የሀገር ባለውለታ አረጋውያንን ማክበር እና መንከባከብ የሁላችንም ድርሻ ነው።

3
አሚኮ “እንክብካቤ እና ዘላቂ ደኀንነት ለአረጋዊያን መልካም ሕይወት” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀንን አክብሯል። በመድረኩ ከተቋሙ ሠራተኞች በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው የተቋማት መሪዎች እና አረጋውያን ተገኝተዋል።
በዕለቱም መዳን ጠቅላላ ሆስፒታል ለአሚኮ ሠራተኞች እና ለአረጋውያን ዕለቱን አስመልክቶ የተለያዩ የጤና ምርመራዎችን አድርጓል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቅርንጫፎች እና ዞኖች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ በቀለ አሰጌ ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት አረጋውያን በተለያዩ የሙያ መስኮች ለሀገሪቱ ትልቅ አበርክቶ ያደረጉ መኾናቸውን አንስተዋል።
አረጋውያን የዕውቀት አባቶች፣ እንደ ማስረጃ የሚያገለግሉ የዕውቀት መዝገቦች፤ በትምህርት የማይገኝ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸው፣ ሀሳብ እና አቅጣጫ መስጠት የሚችሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አሚኮ ቀኑን ያከበረው እነዚህን አባቶች እና እናቶች ማክበር አስፈላጊ መኾኑን ከግምት አስገብቶ ነው ብለዋል። አረጋውያንን ከጥቃት መጠበቅ፣ ጧሪ የሌላቸውን መደገፍ፣ ሕክምና እንዲያገኙ ማገዝ እንደሚያስፈልግ እና አሚኮም እንደ ሚዲያ ተቋም መብቶቻቸው እንዲከበሩ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ቤተሰብ ጉዳይ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር መንበሩ የወርቅ በመድረኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተዋል።
ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መምጣቱን አስታውሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራቱ ለአረጋውያን ትኩረት እንዲሰጡ በመምሪያው ማስቀመጡንም አንስተዋል። ዘንድሮም ሀገራት ለአረጋውያን እንክብካቤ እና ሁለንተናዊ ዘላቂ ደኅንነት ትኩረት እንዲሰጡ ለማሳሰብ በመሪ መልዕክቱ መሠረት እንዲከበር መደረጉን ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ አረጋውያን የሚባለው ዕድሜው 60 እና ከዚያ በላይ የኾነ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ይህ ማለት ግን ሁሉም መሥራት አይችሉም ማለት አይደለም ብለዋል። ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩላቸው መሥራት እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።
የመዳን ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ አቤል ሉሌ ሆስፒታሉ ሥራ የጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢኾንም የሀገር ባለውለታ የኾኑ አረጋውያንን በመደገፍ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያም የተለያዩ የጤና ምርመራዎችን በነጻ ሲሰጥ መቆየቱን እና አረጋውያን ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አረጋግጠዋል። ዛሬም ቀኑን ምክንያት በማድረግ የደም ግፊት እና የስኳር መጠን ነጻ ምርመራ መስጠቱን ተናግረዋል።
አሁን ያለው ዘመን ሥነ ምግባር የተጓደለበት በመኾኑ ወጣቱ ትውልድ ከአረጋውያን በጎ ልምድ እና ዕውቀቶችን ሊቀስም ይገባል ያሉት ደግሞ በዕለቱ ያነጋገርናቸው አረጋውያን ናቸው።
በኢትዮጵያ የጡረታ መውጫ ጊዜ ያጠረ መኾኑ መሥራት የሚችሉ ብዙ ዜጎች ተጧሪ እንዲኾኑ፤ ከወጣቶች ጋር እንዳይገናኙ እና ልምድ እንዳይጋሩ እያደረገ በመኾኑ መንግሥት መሥራት የሚችሉ ሰዎችን የጡረታ ጊዜ እያራዘመ እንዲሠሩ የማድረግ እንዲሁም የጡረታ መውጫ ዕድሜውን ማስተካከል እንዳለበት ሃሳብ ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልእክት፦