“ሹመት ኢትዮጵያን ወደ ሥልጣኔ ጉዞ ለማስኬድ ከፍተኛ ጥረት የምናደርግበት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

19
ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ሥብሠባውን እያካሄደ ነው። በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቀጣይ በሚኒስትርነት ሀገር ያገለግላሉ ያሏቸውን ሚኒስትሮች ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅላቸው አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) የመደመር መንግሥት ካብኔያቸውን ለምክር ቤቱ በእጩነት ያቀረቡት ከትምህርት ዝግጅታቸው ባሻገር የመፈጸም፤ የመከታተል እና በሥነ ምግባር ያላቸውን አፈጻጸም መሠረት በማድረግ እንደኾነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔአቸውን ሲያዋቅሩ በሥራ ልምዳቸው የተሻለ አፈጻጸም ያሥመዘገቡ፤ በቀጣዩ አምስት ዓመታት በትጋት መሥራት የሚችሉ፤ የሕዝብን አደራ መወጣት የሚችሉ፤ ሕዝብ አብዝቶ የሚጠይቀውን ሙስናን የሚጠየፉ፤ ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ፤ ሕዝብን ማገልገል መታደል እና ጸጋ ነው ብለው የሚያምኑ መኾናቸውን ለማረጋገጥ ተሞክሯል ነው ያሉት።
የመደመር መንግሥት እስከ 2050 የሚዘልቅ ግራንድ ስትራቴጂ ዕቅድን አቅዷል። ይህንን ዕቅድ የተረዱ እና የተገነዘቡ መኾናቸው መሠረት ተደርጎ በእጩነት ቀርበዋልም ብለዋል።
የሕዝብን ጥቅም የሚያረጋግጡ እንዲኾኑ ጥረት ተደርጓልም ነው ያሉት። በእጩዎች መረጣ ላይ የብሔር እና የጾታ ሥብጥርን ለመጠበቅ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል።
የካቢኔ እጩ አባላት መሾም ሸክም መኾኑን እንዲገነዘቡ አሳስበዋል። ሹመት የምንዝናናበት ሳይኾን የምንፈጋበት፤ የምንሠራበት ኢትዮጵያን ለማጽናት፤ ለማበልጸግ እና ወደ ሥልጣኔ ጉዞ ለማስኬድ ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት የሥራ መስክ መኾኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ሥብሠባውን እያካሄደ ነው።
Next articleየኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እጩ ኾነው የቀረቡት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ማን ናቸው?