‎የትልቅ ሕዝብ፣ ትልቅ ሀገር፤ ታላቅ ርዕይ፦ ዘመናትን የተሻገረ ሥነ መንግሥት ምሥረታ

12
‎‎ረጅም ዘመናትን የተሻገረ፤ በትውልድ ቅብብሎሽ የዳበረ እና በታሪክ ማኅደር በደማቅ ቀለም የተጻፈ የሥነ መንግሥት ምሥረታ የቆየ እርሾ ያለው ሕዝብ ነው የአማራ ሕዝብ።
‎የዚህ ሕዝብ የሥርዓተ መንግሥት ምሥረታ የቆየ ልምድ ሕግ እና ሥርዓት የነገሡበት፣ የሕዝብ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በተቋማዊ አሠራር የሚመሩበት የጸና ሥርዓት እንደሚያስፈልግ በጥልቅ ከመረዳት የመጣም ነው። ይህ ልምድ ዘመናትን ተሻግሯል፤ ዛሬም በተግባር ተረጋግጧል።
‎
‎በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ድምጹን በሰላማዊ መንገድ በመስጠት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያሳየው አጋርነትም ለዚህ ማሳያ ነው። ምርጫውን ተከትሎ የአማራ ክልል አዲስ የመንግሥት ምሥረታ አካሂዷል።
‎
‎በአዲሱ የመንግሥት ምሥረታ በአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ኾነው በድጋሜ የተሾሙት አቶ አረጋ ከበደ በቃለ መሃላ ንግግራቸው፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለክልሉ እና ለሀገሪቱ አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍን የከፈተ፤ የአማራ ሕዝብን የዳበረ የሥነ መንግሥት ታሪክ ባለቤትነት እና ሰላም ወዳድነት ለዓለም ያስመሰከረበት ታሪካዊ ኹነት መኾኑን ተናግረዋል።
‎
‎ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ መንግሥት በክልሉ ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚሠሩ የፖለቲካ እና የሕግ ማስከበር ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ጠንክሮ ይሠራል ብለዋል። የኢኮኖሚ ጥገኝነትን በመቀነስ በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል በማመቻቸት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲኾኑም ይሠራል ነው ያሉት።
‎
‎የክልሉ መንግሥት ትኩረቱን በተጨባጭ ሀብት በሚፈጥሩ፤ የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ትርጉም ባለው መልኩ በሚያሻሽሉ የአምራች ኢንዱስትሪ፣ ዘመናዊ ቱሪዝም፣ ዘመናዊ ግብርና፣ ማዕድን ሃብት ልማት፣ ጤና እና ትምህርት ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
‎
‎በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የክልሉ መንግሥት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በዝርዝርም አቅርበዋል። የታቀዱ ተግባራት በውጤታማነት እንዲፈጸሙ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የማሳተፍ ሥራም ይከናወናል ነው ያሉት። ይህ እቅድ እንዲሳካ ከክልሉ ነዋሪዎች ምን ይጠበቃል ብለው ያስባሉ? ሀሳብዎን ያጋሩን👇
‎
‎
‎በአድኖ ማርቆስ
‎
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ሹመት አጸደቀ።