
“በጫካ ለምትገኙ ታጣቂዎች ደም መፋሰስ እና ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ችግሮች በሰላም እና በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ እናቀርብላችኋለን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን መሥራች ጉባኤውን እያካሄደ ነው። ምክር ቤቱ አቶ አረጋ ከበደን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አድርጎ በድጋሜ ሹሟል።
ከሹመታቸው በኋላ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል መንግሥት የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ አቅዶ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የታቀደው ዕቅድ እንዲሳካ ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንፈልጋለን ነው ያሉት። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው ፖለቲካ በንቃት እንዲሳተፉ በመደረጉ የክልሉ መንግሥት ደስተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
ይህ ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ያላቸውን ሃሳብ ለሀገር ሰላም፣ ለዴሞክራሲ እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል። በትብብር እና በፉክክር መካከል ያለውን ሚዛን በማስጠበቅ የሕዝብን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ ከክልሉ መንግሥት ጋር አብረው እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ እና ባለሃብቶች የኢኮኖሚ መሠረት መኾናቸውንም ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ተሳትፏቸውን በማስፋትም ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል። በግጭት በወደሙ አካባቢዎች መልሶ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለይቅርታ እና ለዕርቅ ትልቅ መሠረት ኾነው እያገለገሉ ነው፤ የእናንተን ቃል ማኅበረሰባችን ይሰማል፣ ያዳምጣል፣ ይተገብራል፣ ዛሬ ክልላችን የእናንተን ምክር፣ የሰላም እሴት ግንባታ ይሻል፣ የሰላም ግንባታችሁን በማጠናከር፣ የሕዝቡን ሥነ ልቡና በመገንባት እህትማማችነት እና ወንድማማችነት እንዲጠናከር እንድትሠሩ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ ብለዋል።
ሀገር የምትመራው በስሜት ሳይኾን በዕውቀት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ምሁራን ለክልሉ ሰላም እና ዕድገት በጥናት የተደገፈ ሥራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል። የመፍትሔ አመንጭነት ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። ምክንያታዊነት እንዲሰፍን እና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ እንዲገነባ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ሴቶች እና ወጣቶችም ለክልሉ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ለሰላም እና ለሀገር ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ክልሉ ባለፉት ዓመታት በግጭት ውስጥ አልፏል፤ በዚህ ውስጥም የታየው በጥላቻ እና ግጭት አሸናፊ አለመኖሩን ነው፤ የጠመንጃ ድምጽ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም እና የሕዝብ መፈናቀል ያመጣል፤ ግጭት ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ የዕድገት እና የመለወጥን ዕድል የሚዘጋ፣ እናቶችን የሚያሳዝን፣ የክልሉን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚ መሠረት የሚያፈርስ እንደኾነም እንገነዘባለን ብለዋል።
በጫካ ለምትገኙ ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ ያለው ደም መፋሰስ እና ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ችግሮች በሰላም እና በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ እናቀርብላችኋለን ነው ያሉት።
ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው በውይይት መኾኑንም ገልጸዋል። በግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶች የግጭት ሰለባ እንዳይኾኑም ጠይቀዋል።
የሚዲያ አካላት የሕዝብ ድምጽ እና የገጽታ ግንባታ ሥራዎቻቸውን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል። የክልሉን ሕዝብ አንድነት እንዲያጠናክሩ፣ ከጥላቻ ንግግር እንዲቆጠቡ እና ሀገራዊ ግንባታን እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
