
ፍርድ ቤቶች የታላቅ ሀገር እና የታላቅ ሕዝብ ወሳኝ ተቋማት ናቸው። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በየደረጃው የሚገኙ የፍርድ ቤት ዳኞች ሀለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ከመስከረም 20/2019 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ ያካሂዳል።
ጉባኤውን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ጉባኤው “የዳኝነት አገልግሎትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ መልዕክት ለ10 ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።ጉባኤው በሕግ ተደግፎ በየዓመቱ የሚካሄድ ነው ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በፍርድ ቤቶች በውሳኔ ጥራት፣ በመወሰን አቅም፣ በመዛግብት ማጣራት ብዛት እና በሁሉም መለኪያዎች እስካሁን ከነበሩት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተዋል።
የፍርድ ቤት ዳኞች ዓመቱን ሙሉ በመዝገብ ሥራ ላይ ቆይተው ያስመዘገቧቸው ትላልቅ ውጤቶች አሉ ነው ያሉት። የተገኘውን የላቀ አፈጻጸም በማስፋት የበለጠ ማላቅ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ይህንን ለማስቀጠል እንዲቻልም ፍርድ ቤቱ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች፣ አዳዲስ አሠራሮች፣ አዲስ በወጡ የሕግ ማቀፎች፣ በውስጥ አሠራር ሥርዓቶች በተመለከተ በጉባኤው ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ለአብነትም በአዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና የማስረጃ፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ፣ በኢንቨስትመንት ሕጎች፣ በመሬት ሕግ፣ በተቋሙ የውስጥ አደረጃጀት፣ በውስጥ አሠራር መመሪያዎች፣ በአዳዲስ የሕግ ማቀፍ እና ፖሊሲዎች ላይ ውይይት የሚደረጉባቸው ርእሰ ጉዳዮች መኾናቸውን አንስተዋል።
በጉባኤው በ2018 በጀት ዓመት በየደረጃው የተገኙት የላቀ አፈጻጸም ተሞክሮዎች ተቀምረው እንደሚቀርቡም አብራርተዋል። የተገኙትን ምርጥ ተሞክሮዎች ለቀጣይ ዓመት ለማስቀጠል፣ ድክመቶችን ለማሻሻል እና በ2019 በጀት ዓመት ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲቻል ዓላማ ያደረገ ጉባኤ መኾኑን አብራርተዋል።
#ታላቅ_ሀገር #ታላቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ
#አሚኮ #Amhara_Region #SupremeCourt #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_19_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
