
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርጓል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዮሐንስ አማረ መንግሥት በአማራ ክልል የማኅበረሰቡ ጥያቄ የነበሩ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል።
በክልሉ ያለውን የሰላም እጦት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ ማኅበረሰቡ አጋዥ መኾን እንዳለበትም ተናግረዋል። የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይኾን የክልሉን ሕዝብ እገዛ ይፈልጋል ብለዋል።
ላለፉት ዓመታት ከባሕር በር ተገልላ የነበረችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትኾን በዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር ጥያቄዎች ትኩረት እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን መንግሥት ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የተሻለ ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያን ከአደጉት ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እየሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
ሀገርን ማስቀደም ይገባል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች መተባበር እና አንድነት አሁን ካለንበት ችግር የሚያወጣ በመኾኑ ትብብራችን ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የቀደሙት አባቶች ልዩነትን በጥበብ በመፍታት ሀገር ማቆም እንደቻሉ ሁሉ የአባቶችን ታሪክ መድገም ከአሁኑ ትውልድ ይጠበቃል ነው ያሉት።
#አሚኮ #ሰላም #ጎንደር_አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ጎንደር #መስከረም_19_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
