
በጤናው ዘርፍ ቁልፍ ከኾኑት ግብዓቶች መካከል የመድኃኒት አቅርቦት አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የመድኃኒት አቅርቦትን ማሳለጥ ሌላኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ባሕር ዳር ቅርንጫፍ በአቅርቦት እና በስርጭት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ውይይት ከደንበኞቹ ጋር አካሂዷል።
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሰሜን ምዕራብ ክላስተር እና የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ አምሳሉ ጫኔ ተቋሙ ጥራታቸው እና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተቋማት እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ተቋሙ ግዥ የሚፈጽመው እና የሚያቀርበው የተቋማትን ፍላጎት መሠረት በማድረግም ነው ብለዋል። የጤና ተቋማት መድኃኒት በፍላጎት ልክ በመውሰድ በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
ችግሩን ለመፍታት የጤና ተቋማት የመድኃኒት በጀታቸውን ከፍ በማድረግ የመድኃኒት ጥያቄያቸውን ማቅረብ እና በስፋት መውሰድ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የሚስተዋሉ ችግሮችን ከደንበኞች ጋር በመነጋገር የአቅርቦት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአማራ ክልል የመድኃኒት ክፍል ኀላፊ ዓለምነው አስፋው እንደተናገሩት ማኅበሩ መድኃኒቶችን ለማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የአቅርቦት ችግሮችን እየፈታ ይገኛል።
የባሕር ዳር አዲስ ዓለም ሆስፒታል የፋርማሲ አስተባባሪ አለበል አበባው የታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እጥረት እንደሚከሰት አንስተዋል። ለዚህም በፍላጎት ልክ ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል የበጀት እጥረት ስለሚያጋጥም ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ግዥ በመፈጸም በቅንጅት በመሥራት በወቅቱ የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑን አመላክተዋል።
#አሚኮ #ጤና #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_19_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
