“በጠንካራ ተቋማት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ያላት ኢትዮጵያን እየገነባን እንቀጥላለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

9
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ትውልድ ተሻጋሪ የፋይናንስ ዐቅምና ኢኮኖሚ እየገነባች ነው ብለዋል።
ዛሬ 2ኛውን የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም (Ethiopia Finance Forum 2026) በዓድዋ ድል መታሰቢያ በይፋ ከፍተናል።
ኢትዮጵያ ለዓመታት ያልተፈቱ የማክሮ-ኢኮኖሚ መዛባቶችን ለመቅረፍ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን ገበያ መር አድርጋለች፤ የገንዘብ ፖሊሲን አዘምናለች፤ የካፒታል ገበያን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ እንደገና አስጀምራለች፤ የፋይናንስ ዘርፏን ለውድድር ክፍት የሚያደርጉ የሕግና የፖሊሲ ሪፎርሞችን አከናውናለች።
በመደመር መንግሥት የተወሰዱ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል። የወጪ ንግዳችን አድጓል፤ የውጭ ምንዛሬና የካፒታል ክምችታችን ተጠናክሯል፤ የዋጋ ንረት ጫና እየቀነሰና ለግሉ ዘርፍ ማነቆ የነበሩ አሠራሮች እየተቀረፉ ይገኛሉ።
የኢኮኖሚ ማሻሻያችን እውነተኛ መለኪያ በዜጎቻችን ሕይወት ላይ የሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥ ነው። ይህም የሚረጋገጠው አርሶ አደሩ፣ ወጣቶች፣ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት አግኝተው ምርታማነታቸውን ማሳደግና ሐሳባቸውን ወደ ታላቅ ንግድ መቀየር ሲችሉ ብቻ ነው።
ለዚህ ስኬት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ወሳኝ ነው። መንግሥት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር ሲዘረጋ፤ ባንኮች፣ ኢንቨስተሮችና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ደግሞ አብሮ ፈጣሪዎች ይሆናሉ።
በጽኑ ዲሲፕሊን፣ በሚያሠራ ፖሊሲ፣ በትጉ አተገባበር እና በጠንካራ ተቋማት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ያላት ኢትዮጵያን እየገነባን እንቀጥላለን።
Previous articleበላይ አርማጭሆ ወረደ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።