
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ እና የደኅንነት ሕልውና የሚረጋገጠው በዓባይ እና በቀይ ባሕር የውኃ ሀብት እንደኾነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት ለማስከበር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በጽናት ገድባ ለፍጻሜ ማብቃቷ ይታወቃል።
አሁን ደግሞ የትኩረት አቅጣጫዋ ከግድቡ ወደ ወደቡ ዞሯል፤ ሀገሪቱ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባሕር በር ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብት ለማስከበር እና በዲፕሎማሲያዊ መርሕ ለማስመለስ በትኩረት እየሠራች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የብዙ ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የኾነችው ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ ታሥራ መቆየት አትችልም። የባሕር በር ማግኘት የሕልውና፣ የፍትሕ እና የተፈጥሮ መብት ጥያቄ እንጂ የሌሎችን ሉዓላዊነት የመጋፋት ፍላጎት አይደለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ፍላጎቷን በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና ሰጥቶ በመቀበል መርሕ መሠረት እንደምታሳካውም መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር በር ባለቤት መኾኗ የቀጣይ እድገቷ እና ሕልውናዋ ወሳኝ መሠረት እንደኾነም ምሁራን ያመላክታሉ።
ይህም ሀገሪቱ በየዓመቱ ለወደብ አገልግሎት የምታወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማስቀረት ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ማዋል እንድትችል ያደርጋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ኢትዮጵያ የቀጥታ የባሕር በር ማግኘቷ በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንድትጫወት ያደርጋታል ብለዋል።
በተለይም በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የሚታዩ የጸጥታ ሥጋቶችን በመከላከል ረገድ ሀገሪቱ የራሷን የባሕር ኃይል በመጠቀም ቀጣናዊ ሰላምን እና ደኅንነትን ለማስከበር ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የባሕር በር ለንግድ ብቻ ሳይኾን ሀገርን ከጥቃት ለመከላከልም ወሳኝ የብሔራዊ ደኅንነት ዓምድ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ የታሪክ እና የተፈጥሮ ባለቤትነቷን መሠረት በማድረግ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳማኝ እና ሕጋዊ ነጥቦችን ማቅረብ እንዳለባት ጠቅሰዋል።
በተለይም የባሕር በር ጥያቄው የቀጣናውን የጋራ ዕድገትና ሰላም የሚያረጋግጥ እንጂ የወረራ ፍላጎት አለመኾኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ለጎረቤት ሀገራት እና ለቀጣናው አካላት በግልጽ ማስረዳት ይገባል።
ለወደብ ባለቤት ሀገራት የኢትዮጵያን ሰፊ የሕዝብ ቁጥር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የአየር መንገድ አገልግሎት እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በወደብ ድርሻ የመቀየር የንግድ አማራጮችን ማቅረብ ሌላኛው መንገድ መኾኑንም ምሁራን ጠቁመዋል።
የሕዳሴ ግድብ በሕዝብ አቅም እና አንድነት እንደተገነባ ሁሉ የባሕር በር መሻትም ሙሉ ሀገራዊ መግባባት እና ድጋፍ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፤ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ የባሕር በር ባለቤትነትም በሀገራዊ አንድነት እንደሚረጋገጥ ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ!
