
የአማራ ክልል ምክር ቤት በተሻሻለው የአደረጃጀት፣ የአሠራር ሥነ ሥርዓት እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ዙሪያ ለሰባተኛው ዙር የምክር ቤት አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የሕዝብን አደራ ተቀብሎ መሥራት ትልቅ ዕድል እና ኀላፊነት መኾኑን ገልጸዋል።
አባላቱ በዋናነት በሕዝብ ውክልና፣ በክትትል እና ቁጥጥር፣ በዕቅዶች ግምገማ እና ማጽደቅ ላይ አተኩረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ባለፈው የስድስተኛው ዙር የምክር ቤት ቆይታ የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩም የሕዝብ ውክልናን በብቃት ከመወጣት እና ከቁጥጥር አፈጻጸም አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት ኀላፊነታቸውን ሲወጡ ከግል እና ከቡድን ወይም ከወገንተኝነት ስሜት በመውጣት ትክክለኛ የሕዝብ ተጠቃሚነትን እና ተሳታፊነትን በሚያረጋግጡ ሕጎች እና አሠራሮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ቃለ መሐላውን በማክበር በመረጣቸው ሕዝብ ዘንድ በአካል በመገኘት ጥያቄዎችን መሠብሠብ፣ በጉባኤ ላይ በንቃት በመሳተፍ የሕዝቡን ድምጽ ማስተጋባት እና በተለይም የሰላም እና የልማት ዕቅዶችን መሥራት እና ማሠራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የወጡ ሕጎች እና የጸደቁ ዕቅዶች የኅብረተሰቡን ችግር በሚፈታ መልኩ መተግበራቸውን በተገቢው መንገድ መከታተል ቁልፍ ተግባራቸው መኾኑንም አስገንዝበዋል።
የምክር ቤት አባልነት ክብር ብቻ ሳይኾን የሕዝብን ጥያቄዎች በሂደት ለመፍታት ቆርጦ መሥራትን የሚጠይቅ ትልቅ ኀላፊነት ጭምር መኾኑን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
