
ኢትዮጵያ የበርካታ ዘመናት ታሪክ ባለቤት ከመኾኗ ባለፈ በብዙ መንገድ የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች። የዚህ ታላቅ ጉዞ ማሳያዎች የኾኑት ትላልቅ ፕሮጀክቶች፣ የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት አቅም ከማሳደግም በላይ የመላው አፍሪካ የኩራት ምንጭ መኾን ችለዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ለትውልድ የሚተላለፉ ትላልቅ የልማት ምዕራፎች ናቸው።
የአፍሪካ ምልክት ከኾኑት ፕሮጄክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንዱ ነው። አፍሪካውያን መሪዎች እና ታዊቂ ሰዎች በጉባ ተሰባስበው ግድቡን ሲመርቁ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካውያን የብርሃን ምንጭ ከመኾኑም አልፎ የኢኮኖሚ ትስስር ሁነኛ መንገድ ነው ብለውታል።
ሌላው ከኢትዮጵያም አልፎ ተምሳሌትነቱ ለአፍሪካ የሚተርፈው ፕሮጀክት የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ነው። አፍሪካን ከቀጣናው እና ከዓለም ጋር በማገናኘት “የሰማይ ንጉሥ” ኾኖ የአህጉሪቱን የንግድ እና የቱሪዝም ትስስር የሚያጠናክር ይኾናል። ይህ ፕሮጄክት በአፍሪካ ወደር የማይገኝለት ኾኖ በፍጥነት እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሥራው ማስጀመሪያ ወቅት ተናግረዋል።
እነዚህን ሁለት ፕሮጄክቶች ለአብነት አነሳን እንጅ ኢትዮጵያ ሌሎችንም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በመገንባት ላይ ናት። የገጠር እና የከተማ ኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለሸገር፣ ለሀገር እና ለትውልድ፣ በማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በጋዝ፣ በነፋስ ኃይል እና በሌሎች መስኮች ግዙፍ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ምጣኔ ሃብትን ከፍ በማድረግ የዜጎችን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ የሀገርን ክብርም የሚያስጠብቁ ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ!
