በሜዳችን የራሳችንን ጨዋታ ተጫውተን ያለንን እንሰጣለን።

11

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ያጠናቀቀ ሲኾን፣ የመጫወቻ ሜዳው ሁኔታ እጅግ ምቹ እንደኾነ እና ስታዲየሙን ላዘጋጁ አካላት በሙሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

በነገው ጨዋታ በረከት ሳሙኤል በጉዳት እንዲሁም መስፍን ታፈሰ በሁለት ቢጫ ካርድ ምክንያት የማይሰለፉ ሲኾን፣ ቀሪዎቹ 21 ተጫዋቾች በመልካም የጤና እና የብቃት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በሁለት ቀን ዝግጅት ብቻ አዲስ ታክቲካዊ ነገር መፍጠር ቢከብድም፣ ተጫዋቾች በሥነ-ልቦና ረገድ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ እንዲኾኑ ተሠርቷል ነው ያሉት።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ግብ ማስቆጠርን ማለማመድ ቀላል አለመኾኑን ያነሱት አሠልጣኙ ዕድሎችን እየፈጠሩ ግብ ማግባት ካልተቻለ ችግሩ የሥነ-ልቦና እንጂ የሲስተም አለመኾኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ ዕድሎችን መፍጠር ባልቻለበት ወቅት ሲስተም እንደሚቀየር ጠቁመው፣ አሁን ላይ ግን ዕድሎች እየተፈጠሩ በመኾናቸው ተጫዋቾች ወደ ግብ አካባቢ ሲደርሱ የመሞከር ሙሉ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ተጫዋቹ ያሬድ ባዬ በበኩሉ ከዚህ ቀደም ከሜዳ ውጭ በሚደረጉ ጨዋታዎች የተጋጣሚ ደጋፊዎችን ጫና ሲቋቋሙ መቆየታቸውን አስታውሶ በባሕር ዳር የሚገኘውን ድንቅ የደጋፊዎች ድጋፍ ተፎካካሪን ለመጫን በአወንታዊ መልኩ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግሯል።

ሴኔጋሎች ለጨዋታው መዘጋጀታቸውን የጠቆሙ ቢኾንም እኛም በበኩላችን ተዘጋጅተናል፤ ማን የተሻለ እንደተዘጋጀ ከጨዋታው በኋላ የሚታይ ይኾናል ነው ያለው።

ሴኔጋል ምንም እንኳ የአፍሪካ አንደኛ ቡድን ቢኾንም፣ በነገው ጨዋታ በገዛ ሜዳችን የምንጫወት በመኾኑ የራሳችንን ጨዋታ ተጫውተን ያለንን ሁሉ ለመስጠት ወደ ሜዳ እንገባለን ብሏል።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_18_2019_ዓ_ም

በጥበቡ ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“በምግብ ራስን መቻል ሉዓላዊነትን የምናረጋግጥበት ግንባር ነው”