
“ፊፊ ስሰማ የምበላውን ምግብ አቋርጫ እየከነፍኩ ጨዋታው ወደአለበት ቦታ እሄዳለሁ፤ ፊፊ አብሮ አደጌ ነው” ይላሉ የጃዊ ወረዳ ፈንድቃ ከተማ ነዋሪው አቶ ንጋቱ ዋሴ።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጃዊ ወረዳ ማኅበረሰብ ዘንድ “ፊፊ” ከድሮ የቆየ ባሕል ነው። “ፊፊ” ማለት “ውጡ እንውጣ” ማለት ነው። ውጡ እንውጣ ለማለት ደግሞ ከበረሃ ሽመል የሚዘጋጁ ሰባት ክፍሎች ያሉት ባሕላዊ የትንፋሽ መጫወቻ መሣሪያ አለ።
መሣሪያው በተለይ ከሐምሌ 5 እስከ መስከረም 21 ባለው ወቅት በስፋት እንደሚዘወተርም አስረድተዋል።
በክረምት ምሽት በሠፈር አለቃ አማካኝነት የፊፊ ድምጽ ሲሰማ፣ ማኅበረሰቡ የጀመረውን ተግባር አቋርጦ ድምጹ ወደተሰማበት ቦታ ይሠበሠባል።
ጨዋታውም ሰባት ወንዶች ሰባቱን የፊፊ መሣሪያዎች ድምጽ አቀነባብረው እየነፉ፣ ከመሐል አንገት ለአንገት ተያይዘው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይከወናል።
ሴቶች ደግሞ በባሕላዊ አልባሳታቸው አምረው እና ደምቀው በዙሪያው በመክበብ ጨዋታውን ያደምቁታል ብለዋል።
ይህም የክረምቱን ረጅም ምሽት ያቀልላል፤ የሕዝቡንም አንድነት እና አብሮነት ያጠናክራል። የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ መነሻ ከጥንት አባቶች ታሪክ ጋር የተያያዘ መኾኑንም አስረድተዋል።
በወቅቱ ሕዝቡን ያስቸግር ከነበረ አስቸጋሪ ጠላት ጋር በሚታገሉበት ጊዜ በድምጽ እንዳይጠራሩ እና ለጠላት እንዳይሰሙ መላ ዘይደው ፊፊን የጥሪ ምልክት አደረጉት።
በዚህም በሜዳ ላይ ተሠባሥበው በመመካከር ጠላትን በጀግንነት ድል ለማድረግ ችለዋል ብለዋል።
በመኾኑም ባሕሉ የአባቶችን አርቆ አስተዋይነት፣ ጥበብ እና በኅብረት የማሸነፍ እሴት የሚያሳይ ታሪክ መኾኑን ጠቁመዋል።
የጃዊ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ በላይነሽ ዓለማየሁ እንደሚገልጹት ይህ ጠላትን በጋራ ድል ያደረጉበት ታሪካዊ ትውፊት ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ የአካባቢው አባቶች እና እናቶች ለወጣቶች እያስተላለፉ ይገኛሉ።
አቶ ንጋቱን ጨምሮ ሌሎች አባቶች እና እናቶች ከጥንት የወረሱትን ይህን ድንቅ ባሕል ጠብቀው ለማቆየት እና በድምቀት ለማከበር እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
#የፊፊጨዋታ #አዊ_አማራክልል #አሚኮ #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_18_2019_ዓ_ም
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
