ከተራ ‘የልጥ መንከሪያነት’ ወደ ቱሪዝም ማዕከልነት የውኃ አካላት ትንሳኤ

9

 

ኢትዮጵያ በውኃ ሃብቷ እና በተፈጥሮ ጸጋዋ እጅግ የበለጸገች ሀገር ናት።

ይሁን እንጂ ለዘመናት ይህንን ጸጋ የምትጠቀምበት ኋላቀር መንገድ “የልጥ መንከሪያ” ከሚለው ብሂል ያልዘለለ ነበር።

በተለይ የከተማ ወንዞች እና የሐይቅ ዳርቻዎች የቆሻሻ መጣያ፣ ለዕይታ የሚዘገንኑ ኾነው ኖረዋል።

አሁን ወንዞች እና ሐይቆች የትኩረት ማዕከል እየኾኑ መጥተዋል።

ያ አሳዛኝ ታሪካቸው ተቀይሮ የሀገሪቱን ታላቅነት በሚመጥን ርዕይ ዳርቻዎቻቸው ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ቅንጡ የመዝናኛ ስፍራዎች እየተቀየሩ ይገኛሉ።

የገጽታ ሽግግሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “እኛ ኢትዮጵያውያን ውኃ ላይ ተቀምጠን በውኃ ጥም የምንሰቃይ፣ በተፈጥሮ ጸጋ ተከበን በድህነት የምንኖር ነን፤ ይህንን የዘመናት ታሪክ በተግባር መቀየር አለብን” በማለት ካስቀመጡት የቁጭት እና የተግባር ርዕይ ይመነጫል። የቁጭት ጉዞው በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ነው እየተገለጠ ያለው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዐይን ካላየ ግንባር ነው” እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብትን አቅም አስቀድሞ በውል በማየት እና ቦታዎችን ለሰዎች ምቹ እና ተወዳጅ በማድረግ የተቃኘው የልማት እርምጃ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የውኃ አካላት ዳርቻዎችን በማጽዳት አተኩሯል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህ ስፍራዎች ዜጎች በንጹሕ አየር የሚዝናኑባቸው ማራኪ የወዳጅነት ፓርኮች እና የከተማ ኮሪደሮች በመኾን የከተሞች ስም የሚመጥን ገጽታ አላብሰዋል።

በተግባር እየተገለጠ ያለው ርዕይ ከከተማ አልፎ ሀገሪቱ ወደ ሸሸገቻቸው ጥልቅ የተፈጥሮ ጸጋዎችም ዘልቋል። የወንጭ ሐይቅ የዚህ የገበታ ለሀገር ልማት አካል ኾኖ ወደ ማራኪ የቱሪስት መዳረሻነት አድጓል።

በመሠረተ ልማት እጥረት ተደብቆ የነበረው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክም በዝሆን ዳስ ሎጅ አማካኝነት የቅንጡ መዝናኛ ማዕከል ኾኗል።

በጊቤ ሦሥት ሰው ሠራሽ ሐይቅ ዳርቻ የሚገኘው ጥንታዊው የሀላላ ኬላም ታሪክን ከተፈጥሮ ጋር አዋህዶ ወደ ደማቅ ሪዞርትነት ተቀይሯል።

የውኃ ዳርቻዎች ትንሣኤ ሌላው ጉልህ ማሳያ ግዙፉን የጣና ሐይቅ ተንተርሶ የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት እና በባሕር ዳር እየተከናወነ ያለው የጣና ዳርቻ ልማት ናቸው።

ግዙፍ ፕሮጀክቶቹ በወሎ ከሚገኘው እና ወደ ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም ማዕከልነት ካደገው ታሪካዊው የሎጎ ሐይቅ እና ከሌሎች የሐይቅ ዳር ፕሮጀክቶች ጋር ተዳምረው ኢትዮጵያ ያላትን ያልተነካ ጸጋ አውጥተው እያሳዩ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ያለባትን ዕዳ እና ችግር ብቻ ሳይኾን ያላትን ጸጋም ማየት አለብን” በማለት እንዳስገነዘቡት የውኃ አካላትን ከቆሻሻ መጣያነት አውጥቶ ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት መቀየር መቻሉ ትልቅ ጉዳይ ነው።

ተግባር ተኮር ልማቱ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ መቼም ቢኾን ተነጣጥለው እንደማይሄዱ በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው።

የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለትውልድ የሚሻገር የውበት፣ የሥነ ልቦና ዕረፍት እና የኢኮኖሚ አቅም መኾን እንደሚችሉ የሚያሳይ ሕያው ምስክርም ነው።

​#AMECO #EthiopiaEcotourism #DineForEthiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_18_2019_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው ተሾሙ።
Next articleወጣቶች የሰላም እና የአንድነት ግንባር ቀደም ዘቦች ሊኾኑ ይገባል።