‎ስፖርት ቱሪዝም – የባሕር ዳር ሌላኛው የኢኮኖሚ አቅም ⚽️

3

 

‎የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርጉት ታላቅ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታ በመጭው ማክሰኞ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይካሄዳል።
‎
‎በዚሁ መሠረት የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ቤተሰቡን እና ደጋፊዎችን በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
‎
‎የቢሮው ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) እንደገለጹት ይህ ጨዋታ የስፖርት ቱሪዝምን በማነቃቃት እና የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እውን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው።
‎
‎ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የካፍ እና የፊፋ መስፈርቶች የሚያሟላ ሜዳ ባለመኖሩ ምክንያት ጨዋታዎቻቸውን ከሀገር ውጭ ለማድረግ ተገድደው እንደነበር አውስተዋል።
‎
‎ምክትል ኀላፊው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ሰፊ የግንባታ ሥራ ስታዲየሙ የካፍን ጊዜያዊ ፈቃድ በማግኘቱ አሁን ላይ ጨዋታዎች በሀገር ውስጥ መካሄድ እንደሚጀምሩ አብራርተዋል።
‎
‎ቀደም ሲል በተካሄዱ ጨዋታዎች ከ100 ሺህ በላይ ታዳሚዎች መታደማቸውን በማስታወስ ዘንድሮም በርካታ እንግዶች ወደ ባሕር ዳር ከተማ እንደሚጎርፉ ይጠበቃል ነው ያሉት።
‎
‎ይህም ሁነት ከትንንሽ ነጋዴዎች እስከ ትልልቅ ሆቴሎች ድረስ ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመፍጠር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።
‎
‎እንግዶችን በአግባቡ ለመቀበል ከታክሲ ማኅበራት፣ ሆቴሎች እና ካፌዎች ጋር ውይይት ተደርጎ ዝግጅት መጠናቀቁ የተገለጸ ሲኾን አስተማማኝ ጸጥታን ከማረጋገጥ ባሻገር የበጎ ፈቃደኞች፣ የሕክምና እና የአምቡላንስ አገልግሎቶችም ተመቻችተዋል።
‎
‎በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ከዋክብት የተሠበሠቡበት የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ወደ ባሕር ዳር መምጣቱ ለጨዋታው ልዩ ድምቀት የሚሰጥ እና ከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መኾኑም ተጠቅሷል።
‎
‎በመኾኑም የከተማዋ ነዋሪ እና ደጋፊው በነቂስ ወጥቶ ስታዲየሙን በመሙላት ዋሊያዎቹን በስፖርታዊ ጨዋነት በመደገፍ ታሪካዊ ድል እንዲመዘገብ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ ቀርቧል።
‎
‎#EthiopiaVsSenegal #BahirDar #SportsTourism #አሚኮ #ኢትዮጵያ🇪🇹
‎
‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
‎
‎ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“እኛ እንደተቀበልነው ሁሉ ጠብቀን እና አልቀን ለተተኪው እናስረክባለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ