በአሁኑ ዘመን ቴክኖሎጂ የቅንጦት ጉዳይ ሳይኾን የሀገራት ብሔራዊ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ መለኪያ ኾኗል። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ጉዞዋን ወደ ዲጂታሉ ዓለም ያደረገችው።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን አቅም በተግባር እያረጋገጠች፣ ለአፍሪካ ኢኖቬሽንም መንገድ እየጠረገች ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት የቴክኖሎጂ ጉዞ ግን ሁሉም ነገር የተመቻቸ አልነበረም። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሀገሪቱ በዘርፉ በርካታ መዋቅራዊ ማነቆዎች ነበሩባት። የቴሌኮም ዘርፉ በአንድ የመንግሥት ተቋም ስር ብቻ በመቆየቱ የኢንተርኔት ተደራሽነት እና ጥራት ዝቅተኛ ነበረ።
የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩም የፋይናንስ ዘርፉ በወረቀት ላይ የተመሠረተ ኾኖ ቆይቷል። ለፈጠራ ሥራዎች የሚኾን ምቹ ሥነ-ምህዳር እና የላቁ ቴክኖሎጂዎችን የሚመሩ ተቋማት አለመኖራቸውም ሀገሪቱን ከዓለም አቀፉ የዲጂታል አብዮት አግልሏት ቆይቷል።
በቅርብ ጊዜ የተወሰዱ የሪፎርም ርምጃዎች ግን ይህንን የዝግመት አዙሪት በመስበር ውጤቶችን እያሳዩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ትላንት ሌሎች የፈጠሩትን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ነበርን፤ ዛሬ ግን የራሳችንን አቅም ገንብተን የነገዋን ታላቅ ኢትዮጵያ በራሳችን ልጆች እጅ እንቀርጻለን” ብለዋል።

የቴሌኮም ዘርፉን ነጻ በማድረግ የኢንተርኔት ተደራሽነትን በፍጥነት ማሳደግም ተችሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን ያፈራው ቴሌብርም የፋይናንስ አካታችነትን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል። በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 4 ነጥብ 19 ትሪሊዮን ብር በቴሌብር መፈጸሙን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል የግብይት ሥርዓትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል “ዘመን ገበያ” የዲጂታል ገበያንም አስጀምሯል። ይህም ከአነስተኛ ንግድ ጀምሮ እስከ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች በማገናኘት፣ የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲጨምር፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እና አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲያድግ እያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የአይሲቲ ፓርክ ማስፋፊያ፣ የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የተካነ የሰው ኀይል ለመፍጠር ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት እና አዲስ የኤ.አይ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋምን ጨምሮ በግዙፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጅማሮዎች አማካኝነት ወጣቶቿን ለወደፊቱ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ኾናለች” በማለት የሀገሪቱን ራዕይ መስክረዋል።

የነገዋ ኢትዮጵያ ራዕይም ቴክኖሎጂን ከኢኮኖሚ ሞተርነት አልፎ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ወደሚያቀል የልዕልና ደረጃ ማሸጋገር ነው። በሰባቱ የጉባ ብስራቶች ውስጥ የተካተተው የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ፕሮጀክትም ሀገሪቱ ከአፍሪካ አልፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ትልቅ የቴክኖሎጂ ምኞት ያሳያል።

ስማርት ከተሞች፣ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ)፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በድሮን የሚታገዝ ዘመናዊ ግብርና፣ ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት እና የዳታ ማዕከላት ግንባታ የነገዋ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ማረጋገጫዎች ናቸው።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው ኢትዮጵያ ነገ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንት እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ማዕከል የሚያደርጉ ናቸው።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው ኢትዮጵያ ነገ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንት እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ማዕከል የሚያደርጉም ናቸው።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ