🏭 የውጭ ምንዛሬው ከሦሥት ዓመት በፊት ከነበረበት በእጥፍ አድጓል።🌟

6

 

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ከቀደምት የባሕላዊ ምርት ስልቶች በማላቀቅ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ወደ ኾነ ዘመናዊ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እያሸጋገረ ይገኛል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከማስፋፋት ባለፈ የጨርቃ ጨርቅ፣ የሲሚንቶ፣ የቆዳ፣ የሌጦ እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች የማምረት አቅምም እያደገ መጥቷል። ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድልም ፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “የኢትዮጵያ ታምርት” እንቅስቃሴዎች ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ሾር ነቀል በኾነ መልኩ በመቀየር ላይ ናቸው ማለታቸው የሚታወስ ነው። ሀገሪቱ በሰፊው ወደ አምራችነት በመሸጋገር ላይ ትገኛለችም ብለዋል። በተለይም ፈተናዎችን አልፎ በተተገበረው ሪፎርም አስደናቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደኾነም ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ልማቱ ከመንግሥት መር ወደ ግል ዘርፍ እንዲሸጋገርም ተደርጓል ነው ያሉት። ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትም የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል፤ በዚህም ከውጭ ይገባ የነበረውን የስንዴ ግዥ እና ለቢራ ብቅል ይወጣ የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

የምርት አቅምን አሟጦ የመጠቀም ሥራ ተሠርቷል። በዚህም ተዘግተው የነበሩ በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል፤ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 67 መቶ አድጓል። የሀገር ውስጥ የፍጆታ ምርቶች ድርሻም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንስተዋል።

የሀገሪቱ የወጭ ንግድ (ኤክስፖርት) አፈጻጸምም ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል ነው ያሉት። የውጭ ምንዛሬውም ከሦሥት ዓመት በፊት ከነበረበት በእጥፍ አድጓል ብለዋል።

ሪፎርሙ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን እግር ከወርች ቀይዷት ከነበረው ውሥብሥብ ችግር ወጥታ ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ከፍታ እየተጓዘች መኾኗን በግልጽ የሚያሳይ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደገለጹት ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ የኢኮኖሚ ድርሻውን ከፍ ለማድረግ እና ተወዳዳሪነቱን ለማረጋገጥ ሰፊ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። በኢንዱስትሪዎች ላይ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ለዘርፉ ትንሣኤ ማረጋገጫ ኾነዋል ብለዋል።

የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከዚህ ቀደም አንድ በመቶ ብቻ የነበረው የብድር ድርሻ ወደ 5 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል ነው ያሉት። በየዓመቱ ወደ ምረት የሚገቡ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታም አድጓል።

የኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት፣ ምርታማነት እና ትርፋማነትም እያደገ ይገኛል። የኢትዮጵያን የንግድ ሚዛን በማሳደግ፤ ዘላቂነትን እና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ አዳዲስ የገበያ አማራጮችን ያካተተ አዲስ የኤክስፖርት ስትራቴጂዎችም እየተለመዱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ጉዞ ፈተናዎች ቢኖሩትም፣ የነገዋን የበለጸገች ሀገር እውን ለማድረግ የተተከለ ጽኑ ምሰሶ ነው። የዚህ የለውጥ ጎዳና ቀጣይነት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና ብልጽግና ትልቅ ዋስትና ነው ።

#አሚኮ #ኢንዱስትሪ #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መሥከረም _12_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleጽዳት፣ ውበት እና ዘመናዊነትን ያስተሳሰረው የኮሪደር ልማት በኢትዮጵያ!
Next articleየግብርና ምርትን ከ44 ሚሊዮን ቶን ወደ 150 ሚሊዮን ቶን ያሳደገው ሪፎርም።