🏘️ “አንችልም” የሚለውን አስተሳሰብ የሰበረው አዲሱ የገጠር ኮሪደር ልማት🇪🇹

9

 

የጥንታዊ ሥልጣኔ ማሕጸን፤ ዘመናትን በጽናት ያሳለፈች፣ ማንነቷን ጠብቃ የዘለቀች ታሪካዊ ሀገር ናት ኢትዮጵያ ።

በየዘመኑ የገጠሟትን ፈተናዎች በጽናት እያለፈች፤ የትናንቱን የክብር ዘመን ለመድገም ወደ ከፍታዋ እየተጓዘች ያለች፤ የብልጽግና ጉዞዋን በቁርጠኝነት እያፋጠነች የምትገኝ ሀገር ናት።

የአክሱም ሐውልቶች ዘመን አይሽሬ የኢንጂነሪንግ ጥበብ፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጀጎል ግንብ የኪነ-ሕንጻ ጥበቦች የትናንቷ ከፍታ ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ የጥበብ ማማዎች፣ የዘመናት ፈተናዎችን ተቋቁመው ዓለምን ያስደነቁ፤ የኢትዮጵያን ታላቅነት ያሳዩ ምስክሮች ናቸው።

ዛሬም ቢኾን የትናንቱን ታሪክ ከነገ የብልጽግና ተስፋ ጋር የሚያስተሳስር እና የሚያጋምድ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት እየተተገበረ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ፤ የሥልጣኔ ባለቤት የኾነውን የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለመቀየር እና የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ መሠረት ለማጽናት እየተከናወነ ያለ ወሳኝ እርምጃ ነው።

ይህ የልማት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን የጥንት አኩሪ ታሪክ በዘመናዊ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ በማዘመን ለተሻለ ነገ ለማሻገር ያለመ ነው። ኢትዮጵያ አቅዳ በመፈጸም፤ አልማ የማሳካት ራዕዩን እውን በማድረግ ትላልቅ ሜጋ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ እያስመሰከረች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ አቅዶ የመፈጸም ባሕልን እያዳበረች የብልጽግና ራዕይዋን በተጨባጭ ምድር ላይ እውን እያደረገች ነው። ሀገሪቱ እያከናወነች የምትገኛቸው ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ የሚያሳዩ የታሪክ አሻራዎች ኾነዋል።

በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ዘመናዊ እና ምቹ የኑሮ ደረጃን በመፍጠር የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘዴ ለማሻሻል ሰፊ ሀገራዊ እንቅስቃሴንም ጀምራለች።

ይህ የገጠር ማሻሻያ ሥራ አርሶ አደሮችን በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ እርምጃ ነው። ይህም አነስተኛ ወጪ በሚጠይቁ፤ በአካባቢው ግብዓቶች የሚገነቡ፤ ነገር ግን ምቹ እና ሞዴል በኾኑ መኖሪያ ቤቶች የአርሶ አደሮችን ሕይወት መለወጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት የገጠር ኮሪደር ልማት ዘመናዊ የእንስሳት ማደሪያዎች፤ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ባዮ ጋዝን በማሟላት ለሕይወት ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችል ነው። በጓሮ የሌማት ቱርፋትን በማልማት የዜጎችን አመጋገብ ማሻሻል እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደኾነ ነው ያስረዱት።

​ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት “እኛ አንችልም” የሚለውን የተሳሳተ የአስተሳሰብ ስብራት በመቀየር በራስ አቅም የመልማት እና በራስ መተማመንን መገንባት ያስቻለ ነውም ብለዋል።

​በሀገር አቀፍ ደረጃ የታቀደውን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቤቶችን ግንባታ ለማሳካት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ዘመናዊ ከተሞችን እና መንደሮችን የመገንባት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው።

“ጸዳ ያለ እና የዜጎቻችንን ኑሮ የሚያዘምኑ ቤቶችን ማብዛት ይኖርብናል” ነው ያሉት። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድንኾን ያስችላል ብለዋል።

“ጀግንነት በጦር መሳሪያ ሳይኾን የድኾችን ቤት መለወጥ እና ሀገርን በማልማት ይለካል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነተኛ ተግባር በቃል ሳይኾን በሥራ የሚረጋገጥ መኾኑን ጠቁመዋል። የነገዋን የለመለመች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

​የምንገነባው ሀገር የየዕለት ውሏችን ውጤት ነው! 🇪🇹

እርስዎስ ይህን ለውጥ እንዴት ይመለከቱታል ?

#ባሕር_ዳር #መስከረም_12_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየምንዛሬ ሥርዓቱን ነጻ ያወጣው የኢኮኖሚ ሪፎርም በኢትዮጵያ!
Next article“የትናንት አባቶቻችን እና እናቶቻችን በደማቸው ጠብቀው ያስረከቡንን ነጻ ሀገር እኛም አጽንተን ለቀጣዩ ትውልድ እናሻግራለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)