ለአባላቱ ደስታን የፈጠረው የመዋቅር ምላሽና አሁንም ያልተመለሰው የተዋረድ ምክር ቤቶች ምርጫ ጉዳይ።

8
የአማራ ክልል ምክር ቤት ከተዋረድ የምክር ቤት አባላት ጋር ሲያካሂድ የቆየውን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አጠናቋል።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ ለሦሥት ቀናት በቆየው መድረክ ከተዋረድ የምክር ቤት አባላት ጋር በ 2018 በጀት ዓመት የነበረውን አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ትውውቅ መካሄዱን ገልጸዋል። በመድረኩ የተዋረድ ምክር ቤት አባላት ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
✍️ የነበሩ ጠንካራ ጎኖች
✅ የኦዲት ግብረ ኀይል በኦዲት የተገኘን ሃብት የማስመለስ አቅም መዳበር
✅ ክትትል እና ቁጥጥር መደረጉ፤
✅ የተጀማመሩ የቴክኖሎጅ ሥራዎች መኖር እና ሌሎች ተሞክሮ የሚወሰድባቸው በመኾናቸው በመድረኩ ቀርበው የልምድ ልውውጥ ተደርጎባቸዋል ነው ያሉት።
የምክር ቤቱ የሥራ አፈጻጸም ጠንካራ እና ደካማ ጎን ለገለልተኛ አካል መቅረቡን ጠቅሰው አጠቃላይ አፈጻጸሙ ሲታይ ውጤታማ መኾኑን ገልጸዋል።
✍️ በበጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶች
🗣ውክልናን ያለመወጣት ክፍተቶች መኖር
🗣የቀበሌ ምክር ቤቶች ጠንካራ ጉባኤ አለማካሄድ፤
🗣 ድጋፍ ላይ የተወሰኑ ጉድለቶች መኖር እንደኾኑ ጠቁመዋል።
7ኛ ዙር የተመረጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የታዩት ክፍተቶችን ማረም እንዳለባቸው አጽንኦት መሰጠቱን ምክትል አፈጉባኤው አንስተዋል።
አስተማማኝ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ክትትል እና ድጋፉን በማጠናከር ምክር ቤቶች አውራ ተቆማት እንዲኾኑ መግባባት ተፈጥሯልም ነው ያሉት።
የምክር ቤቶች መዋቅር በአባላቱ ይነሳ የነበረ አንዱ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ አማረ በክልሉ መንግሥት ምላሽ በማግኘቱ በአባላቱ ዘንድ ደስታን ፈጥሯል ብለዋል። ይህም አባላቱ በተሻለ መንገድ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
ሌላው ያነሱት ጉዳይ የተዋረድ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ጉዳይ ሲኾን ለ14 ዓመታት ሳይካሄድ በመቆየቱ በክልል ምክር ቤቱ ሥራ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ምርጫ ቦርድ እና የክልል ምክር ቤት ባሉበት ውይይት መደረጉንም ጠቁመዋል።
ምርጫውን ዘንድሮ እናካሂዳለን የሚል ስምምነት መፈጠሩን ጠቁመው ነገር ግን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚመራ ነው ብለዋል። በዚህ ዓመት ይደረጋል የሚል ዕምነት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።
መድረኩ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የተዋረድ ምክር ቤቶች ዕውቅና እና ሽልማት በመስጠት ተጠናቋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ጋሪ ወሮ” የቦሮ ሺናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል እየተከበረ ነው።
Next articleበደብረ ታቦር ከተማ የመስቀል በዓል ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።