
የቦሮ-ሺናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል የኾነው “ጋሪ ወሮ” በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው። በበዓሉ አከባበር ላይ የቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የቦሮ-ሺናሻ ብሔረሰብ ተወላጆች እና ሌሎችም ተጋባዦች ተገኝተዋል።
የበዓሉ አከባበር በአባቶች ምርቃት፣ ችቦ በመለኮስ “ዎሮ-ዎሮ” ወይም እንቁጣጣሽ በመባባል ነው መከበር የተጀመረው።
“ጋሪ ወሮ” ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ ሁለት ሳምንት ባሉት ቀናት የክረምት ወቅት አብቅቶ የፀደይ ወቅት ሲገባ መስከረም ወር አጋማሽ ላይ የሚከበር “የጋሮ አደባባይ” ላይ ነው የሚከበረው።
በዕለቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉት የቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ “ጋሪ ወሮ” የይቅርታ፣ የተስፋ፣ የአብሮነት፣ የምስጋ እና የማኅበራዊ መስተጋብር የማንንት ማሳያ ነው ብለዋል።
በዓሉን ይበልጥ ለማስተዋወቅ በአሶሳ ከተማ የባሕል ማዕከል ግንባታ ለማካሄድ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲኾን የሁሉም መዲና በኾነችው አዲስ አበባ በዓሉ መከበሩ ተወላጆችን እርስ በርስ ከማስተዋወቅ ባሻገር ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ያግዛል ነው ያሉት።
የኢፌዴሪ የባሕልና ስፓርት ሚኒስቴር ተወካይ ከፍያለው አብዲሳ የኢትዮጵያ ብዝኀ ባሕሎች እና ማንነቶችን በማስተዋወቅ ኅብረ ብሔራዊት ሀገርን ለመገንባት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
ጋሪ ወሮን ጨምሮ የተለያዩ ብሔረሰቦችን የዘመን መለወጫዎች በብዝኀ ማንነት መገለጫነት ጠብቆ በማቆየት ለማስተዋወቅ የተለያዩ ተግባራት እየተከናዎኑ ነው ብለዋል።
በዕለቱ በዓሉን የሚገልጹ ባሕላዊ ጭፈራዎች እና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል። በዓሉ “ጋሪ ወሮ ለአብሮነት እና ለባሕል ልማት” በሚል መልእክት ነው ለአራተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ የተከበረው።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ
