
“አይቼሽ፣ አይቼሽ ተመልክቼሻለሁ
እቴ በአምባ ማርያም በእሷ ይዤሻለሁ…” በማለት ድምጻዊ ይሁኔ በላይ “ጉዛራ” በተሰኘው ተወዳጅ ዜማው ጠቅሷታል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ቢኾን በፍቅር እና በክብረት “የአምባይቱ እመቤት” እያሉ ይጠሯታል፤ ታሪካዊቷን አምባ ማርያም ገዳም።
አምባ ማርያም ገዳም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ከእንፍራዝ ከተማ ጥቂት ራቅ ብላ በምትገኘው ስሁርሳር ውኃ ቀበሌ ትገኛለች።
ከሰማይ በታች፤ ከተራራው በላይ ኾና የጣናን ሐይቅ ውበት ቁልቁል በስፋት ለምትቃኝበት ለዚች ጥንታዊት ገዳም ተፈጥሮ እና ታሪክ ድንቅ ውበትን አድለዋታል። የታሪክ እና የእምነት ጥምረት ማዕከልም ናት።
👉 የመሥራቹ አጼ ዳዊት አሠራር እና ታሪካዊ መነሻ !
የታሪክ ድርሳናት እንደሚነግሩን አምባ ማርያም ገዳም በ1391 ዓ.ም በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የተመሠረተች ታሪካዊ ገዳም ናት። በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቤተ መጻሕፍት ቡድን መሪ የኾኑት ግርማቸው ሙሉጌታ እንደሚያስረዱት ገዳሟ በጎንደር ዘመን በእንቁላል ቅርጽ ከተሠሩ የኪነ ሕንጻ ሥራዎች አንዷ ናት ብለዋል።
ከጎንደር ከተማ በ62 ኪሎ ሜትር፤ ከጣና ሐይቅ በ9 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከጉዛራ ቤተ መንግሥት በ4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። በቦታው ላይ አጼ ዳዊት ያስገነቡት የመዋኛ ገንዳ ዛሬም ድረስ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ እንደሚገኝም ገልጸውልናል።
ገዳሟ ተራራ ላይ የተሠራችበት ዋነኛ ምክንያት የታላቋን ግሸን ደብረ ከርቤ አምሳያ ለመፍጠር ታስቦ እንደኾነ የሚነገር ሲኾን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእስራኤል ተሰድዳ ወደ ኢትዮጵያ በመጣችበት ወቅት ያረፈችበት የጻድቅ ማረፊያ እንደኾነችም ይነገራል ነው ያሉት ቡድን መሪው።
👉 የግማደ መስቀሉ ማረፊያ እና ሃይማኖታዊ ክብሯ !
የአምባ ማርያም ገዳም ሌላው ድንቅ ታሪክ የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ከመሄዱ በፊት በዚሁ ገዳም ውስጥ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ያህል መቆየቱ እንደኾነ የገዳሟ ታሪክ ያስረዳል። በመኾኑም በግሸን ደብረ ከርቤ የጌታችን ግማደ መስቀል ያረፈበት በዓል በሚከበርበት ሁኔታ በዚች ገዳምም መስከረም 21 ቀን የማርያም መታሰቢያ የንግሥና ዓመታዊ በዓል በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪው ጌታሰው ታደለ በገዳሙ ውስጥ በርካታ መነኮሳት ይኖሩ እንደነበር እና የመኖሪያ ቤቶቻቸው ፍርስራሾች ዛሬም ድረስ እንዳሉ ገልጸዋል። ከ350 በላይ በድንጋይ የተሠሩ ጥንታዊ የመነኮሳት መኖሪያ ባዕት ይገኛሉም ብለዋል።
👉 ተፈጥሯዊ ማራኪነቷ እና አሁናዊ ገጽታዋ !
አምባ ማርያም ገዳም ሁለት መግቢያ በሮች ብቻ ያሏት ሲኾን በዙሪያዋ ባለው አረንጓዴ ደን ተሸፍና በርካታ የዱር እንስሳትን እና የአዕዋፍ ዝርያዎችን አቅፋ ይዛለች።
በአሁኑ ወቅት በአጼ ዳዊት ዋና ቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ላይ እድሳት የተደረገላት ሲኾን የደብር ሙዚየም፣ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እና ቅዱሳት ንዋያትን ያቀፈች የእምነት ቱሪዝም ማዕከል ኾና አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ አቶ ጌታሰው ታደለ ተናግረዋል።
ለጎብኝዎች እንዲመችም የመንገድ መሠረተ ልማት እና የመብራት አገልግሎት ተሟልቶላታል ነው ያሉት።
አምባ ማርያም—መንፈሳዊ ረፍት ለሚሹ፤ የተፈጥሮን ውበት በጣና ሐይቅ ዳር ማየት ለሚሹ ሁሉ ኹነኛ የኢትዮጵያ ሀብት ናት። ቦታው ታሪክ እና የመንፈሳዊነትን አጣምሮ የያዘ የቱሪዝም ሃብትም ነው።
#አሚኮ #Tourism #Ethiopia
#ባሕር_ዳር #መስከረም_10_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
