
ሰዎች የተለያዩ ጉዳዮችን ለማሥፈጸም ከቦታ ቦታ በየብስ፤ በአየር እና በባሕር ትራንስፖርት ይጓዛሉ። እኔም በቅርቡ የሥራ ጉዳይ ገጥሞኝ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ የአየር መንገድን ተጠቀምኩ።
አውሮፕላን ውስጥ ወጣት የገጠር ልጅ ከጎን በኩል ካለው ወንበር ላይ ተቀምጣለች። በአውሮፕላን ጉዞ ስታደርግ የመጀመሪያ ጊዜ መኾኑ በግልጽ ያስታውቅባታል። በጉዞ መሐል ስለ አካባቢዋ፤ ስለ እድገቷ እና ስለምትጓዝበት ጉዳይ አጫወተችኝ።
ባለታሪኳ ወጣት ዓለምነሽ ንጋቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆቿን ለማገዝ አዲስ አበባ በቤት ሠራተኝነት ለማገልገል እየተጓዘች መኾኑን ነገረችኝ። የአውሮፕላን ጉዞ ምቹ ቢኾንም የየብስ ትራንስፖርት ግን ከወጭ አኳያ የምትመርጠው መኾኑን ወጣቷ አጫወተችኝ።
በጸጥታ ችግር ምክንያት በየብስ ትራንስፖርት መጠቀም ስጋት የፈጠረባቸው ወላጆቿ ከሰዎች ተበድረው የአውሮፕላን ትኬት ከፍለውላታል። የአውሮፕላን የትኬት ዋጋ ሠርታ ለቤተሰቦቿ እንደምትመልስም አነሳችልኝ።
“የሕይወት ጉዞዬ ዕዳ በመክፈል ይጀምራል” ያለችኝ ወጣቷ ለወራት ያህል ምንም ተቀማጭ ገንዘብ ሳይኖራት እየሠራች ብድር ልትመልስ ነው።
በዚች ወጣት ታሪክ ውስጥ የሚታየው የሰላም እጦት በሰዎች እንቅስቃሴ እና ሕይወት ላይ አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለ መኾኑን ነው።
በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች ማኅበረሰቡ ከቦታ ቦታ የየብስ ትራንስፖርት ተጠቅሞ እንዳይንቀሳቀስ ስጋት ፈጥሯል። ከሌለው ሃብት እየቀነሰ ለአውሮፕላን ትኬት ወጭ እየተዳረገም ነው። ይህም በማኅበረሰቡ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ከማሳደርም በላይ እንደልብ ተንቀሳቅሶ የመጠያየቅ ማኅበራዊ ሕይወትን እያላላ ነው።
ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ላለማቋረጥ፤ ሕክምና ፈላጊዎች የተሻለ ሕክምና ለማግኘት፤ ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ጉዳይ ለማሥፈጸም ጉዙ ሲያቅድ በየብስ ትራንስፖርት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍራት በአውሮፕላን መጓዝ የግዴታ ምርጫ እየኾነ ነው።
የቻለው በራሱ፤ ያልቻለው ደግሞ ተበድሮም ቢኾን ይጓዛል። የሰላም እጦት የንጹሐንን ሕይወት ከመቅጠፍ፤ የአካል ጉዳት ከማድረሱ እና ቁሳዊ ውድመትን ከማስከተሉ ባሻገር የኢኮኖሚ ኪሳራን በማድረስ የሕዝብን ችግር አራዝሟል።
ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳይኾኑ፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ፤ ገበሬ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዳያገኝ፤ ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ እንዳያቀርብ፤ እናት በልጆቿ ናፍቆት እና ሞት እንድትሰቃይ አድርጓል።
በአዲሱ ዓመት ሰላምን በማጽናት፤ ውይይትን በማስቀደም፤ በየብስ መንገዶች ላይ የሚፈጸም እገታ፤ ዘረፋ እና ግድያን ማኅበረሰቡ በመታገል እና በማስቆም ነጻ የሕዝብ እንቅስቃሴዎችን ማመቻቸት ይገባል።
በአፈሙዝ ችግር እንጅ መፍትሔ አይመጣም እና ሰላምን ማጽናት፤ ውይይትን ማስቀደም፤ የሕዝብን ሰቆቃ ማስቀረት ከሁሉም የሚጠበቅ ከግጭት መውጫ መንገድ ነው።
#አሚኮ #peace #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_10_2019_ዓ_ም
በያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
