በሀረሪ ክልል ከ352 ሺህ በላይ ዜጎች የነፃ ሕክምና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

7

 

በሀረሪ ክልል በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ352 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር አብዲ አሚን ገልጸዋል።

በሀረሪ ክልል በሁሉም የመንግሥት እና በተመረጡ የግል ጤና ተቋማት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ሲሰጥ የነበረው የነጻ ሕክምና አገልግሎት ተጠናቋል።

የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር አብዲ አሚን እንዳስታወቁት መርሀ ግብሩ የልብ ቀዶ ጥገና፣ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የቲቢ፣ ከአንገት በላይ፣ የቆዳ እና የዐይን እንዲሁም ሌሎች ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።

ቀዶ ጥገናን ጨምሮ የአልትራሳውንድና የኤክስሬይ አገልግሎትን ባካተተ መልኩ የተሰጠው አገልግሎትም በገንዘብ ሲተመን 90 ሚሊየን የሚገመት ነጻ ሕክምና አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በመርሀ ግብሩ በተለይ ከፍለው መታከም የማይችሉ አቅመ ደካማ እና ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

መርሃ ግብሩ ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞች ምክንያት የሚከሰተውን ሞት እንዲቀንስ ከማገዝ ባሻገር ኅብረተሰቡ ወደ ጤና ተቋማት ሄዶ የመታከም ልማድ እየጎለበተ መምጣቱ የታየበት ነው ብለዋል።

ምርመራ ከተደርገላቸው መካከል 6.3 በመቶ የሚሆኑት ሳያውቁ የነበረባቸው የጤና እክሎች እንዳለባቸው ተለይቶ ወደ ተገቢው ሕክምና እንዲገቡ ተድርጓል ብለዋል።

በቀጣይም አቅመ ደካማ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የነፃ ምርመራ እና ሕክምና ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ለነፃ ሕክምና መርሀ ግብሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ በጎ ፍቋደኛ ባለሞያዎች፣ ለመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

#አሚኮ #Harar #Ethiopia
ባሕር ዳር #መስከረም10/2019 ዓ.ም

Previous articleየእናቶች እንባ ሊታበስ፣ የአባቶች ተማጽኖ ፍሬ ሊያፈራ እና ሕዝብም እፎይ ሊል ይኾን?