
ግጭት እና ጦርነት ከግለሰብ እስከ ሀገር ድረስ አውዳሚ ነው። የማኅበራዊ እና ሰብዓዊ ቀውስን ያመጣል። የዜጎችን ማኅበራዊ እረፍት ይነሳል፤ ከመኖሪያቸው ያፈናቅላል፤ ከባድ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።
በጎረቤት ሀገር ሱዳን፣ በየመን፣ በሶሪያ እና በሌሎችም ሀገራት የታዩት ግጭቶች እና ያስከተሉት ውጤቶች ለዚህ አስረጂዎችና እና ተግባራዊ ማሳያዎች ናቸው።
🛑ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል በዘለቀው ግጭትም የሰዎችን ሕይወት ተቀጥፏል። የሕዝብ ሃብት እና ንብረት ወድሟል፣ የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ ተገትቷል፣ የማኅበራዊ መሥተጋብር ታውኳል፤ ዘርፈ ብዙ ኪሳራን አስከትሏል።
በክልሉ ሠላም እንዲመጣ የሃይማኖት አባቶች ተማጽነዋል፤ እናቶች አልቅሰው ለምነዋል፤ መንግሥትም በተደጋጋሚ የሠላም ጥሪ አቅርቧል፤ ለታጠቁ ኀይሎችም የምህረት ዕድሎች ተዘርግተዋል። 📢
በዚህም በተሳሳተ መንገድ ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው የቆዩት ታጣቂዎች ግጭት አክሳሪ መኾኑን በጊዜ ሂደት እየተረዱት ነው። መንግሥት የዘረጋውን የሠላም አማራጭ በመቀበል የሚገቡት የታጣቂዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
በርካታ ታጣቂዎች እና የታጣቂ መሪዎችም የጦርነትን አውዳሚነት ተገንዝበው፣ ሠላምን መርጠዋል። ጥያቄዎቻቸውን በሠላማዊ መንገድ ለማቅረብ ወስነው በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ እስከመሳተፍ መድረሳቸው ለዚህ ማሳያ ነው።
የእናቶች እንባ ሊታበስ፣ የአባቶች ተማጽኖ ፍሬ ሊያፈራ፣ በሠላም ወጥቶ መግባት ቅንጦት ሳይኾን መደበኛ የሕይወት ሂደት የሚኾንበት የተስፋ ጭላንጭል በአዲሱ ዓመት መታየት ጀምሯል።🕊️
🌅 በአዲሱ ዓመትም “ግጭቱ አብቅቶ በሰላም ይደምደም፤ በየጫካው ያለው መሳሪያው ይሰብሰብ፤ ሕዝብም እፎይ ይበል” የሚለው የብዙኃኑ ምኞት እና ተስፋ ነው።
ከሰሞኑ በተለይም በሰሜን ጎንደር፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር እና በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የሠላም አማራጭን ተቀብለው በርካታ ታጣቂዎች ገብተዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለዓመታት በጫካ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የቀድሞ ታጣቂዎች የሕዝብን ጥያቄ “እናስመልሳለን” ብለው ወደ ጫካ መግባታቸው የተሳሳተ እንደነበር ተናግረዋል።
“ወጣቶች አድገው ሳይጨርሱ ዓላማ በሌለው ግጭት እንዳያልቁ፤ የተማረው በዕውቀቱ፣ ያልተማረው በጉልበቱ ሠርቶ እንዲያድር ሰላም ወሳኝ” መኾኑን ይገልጻሉ። ይህንን በመገንዘብ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀው ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይወታቸውን እየኖሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች እንደገለጹት እርስ በርስ በመገዳደል የሚገኝ ጥቅም እና የሚመለስ የሕዝብ ጥያቄ እንደሌለ ተረድተው የሰላም አማራጭን መርጠዋል። በቀደመ ድርጊታቸው መጸጸታቸውንም ተናግረዋል። የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ እና የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ነው የተናገሩት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አሁን ያለውን ሰላም ማጠናከር፣ የጸጥታ ኃይሉን የበለጠ ማገዝ እና በቁርጠኝነት መሥራት የ2019 በጀት ዓመት ዋነኛ ተግባር መኾን እንዳለበት እስገንዝበዋል።🎯
#አሚኮ #peace #Ethiopia
#ባሕር_ዳር #መስከረም_10_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
