ከ553 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ አማራ ክልል ገብተዋል።

5

 

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ከርእሰ መሥተዳድሩ በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ክልሉ ገጥሞት ከነበረው የጸጥታ ችግር እየተረጋጋ በመምጣቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ከፍ እንዲል አድርጓል ብለዋል። ወደ ክልሉ የሚገቡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ከ3 ሺህ 900 በላይ ባለሀብቶች መቀበላቸውን አስታውቀዋል። ወደ ክልሉ የገቡት ባለሀብቶች ከ553 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያስመዘገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግ መሠራቱንም ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 59 ነጥብ 2 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው በ2018 በጀት ዓመት 65 በመቶ የማምረት አቅም መድረሳቸውን ነው የተናገሩት። በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም 70 በመቶ እና ከዚያ በላይ ለማድረስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች እየፈታ መኾኑን ተናግረዋል። የክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት እና የኢንዱስትሪ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ከ174 በላይ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት የአማራች እንዱስትሪዎችን ችግር እየፈታ በመኾኑ ምርታማነት ላይ እድገት እየመጣ ነው ብለዋል።

በ2019 በጀት ዓመት ምርታማነትን ማሳደግ፣ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ወደ ክልሉ እንዲመጣ ማድረግ እና አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚገጥማቸውን ችግሮች መፍታት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በክልሉ የሚገኙ አምራች እንዱስትሪዎችን እየጎበኙ፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች እየለዩ፤ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እያስቀመጡ መኾናቸውን ተናግረዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎችን እየተንቀሳቀሱ መጎብኘት እና ለችግሮች መፍትሔ ማስቀመጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ እያደረጉ ያሉት ጉብኝት እና እያስቀመጡት ያለው አቅጣጫ ለኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ትልቅ አቅም መኾኑንም ተናግረዋል።

#አሚኮ #ኢንቨስትመንት #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_09_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ።
Next article“ለዘላቂ ሰላም ሴቶች የእናትነት ጥበባቸውን መጠቀም አለባቸው” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)