
የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ያለመ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) በክልሉ ሰላምን ለማስፈን እናቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በትኩረት ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ይህም ለሀገር ሰላም ግንባታ እና እድገት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አጉልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሴቶች የሰላም መሠረት እና የሀገር ምሰሶ በመኾን የፍቅር እና የተስፋ ዘርን ሲዘሩ እንደነበርም አንስተዋል። የሰላም መደፍረስን በመታገል ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ነው ያሉት። “ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ሴቶች የእናትነት ጥበባቸውን መጠቀም አለባቸው” ብለዋል።
ወጣቶች የሀገር ተረካቢዎች የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ባለቤቶች በመኾናቸው ሀገራቸውን በብቃት በመገንባት ወደፊት ማሻገር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ማኅበራዊ እሴቶችን በማስጠበቅ፤ ኅብረተሰቡን በመምከር እና በማስተባበር ረገድ የነበራቸውን ሰፊ አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
ከደብረ ማርቆስ ከተማ የመጡት የሰላም እናት እመቤት አንዷለም እና ከአንክሻ ጓጉሳ ወረዳ ግምጃ ቤት ከተማ የመጡት የሰላም እናት አልጋነሽ አስፋው በአካባቢያቸው ሴቶችን በማደራጀት ሰላምን ለማስፈን ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። ሴቶች ሁሉ የሰላም አምባሳደር መኾን አለብንም ብለዋል።
#አሚኮ #ሰላም #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_09_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
