‎”ሜሪቶክራሲ መጽሐፍ” ለዘመናዊ ሀገረ-መንግሥት ምስረታ አዲስ ኮምፓስ

7


‎በደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የተጻፈው “ሜሪቶክራሲ” መጽሐፍ የምረቃ መርሐ ግብር በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።

‎በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረማርያም የአንድ ሀገር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ስኬት የሚለካው ለማኅበረሰባዊ ሁለንተናዊ ስኬት እና እድገት የአንበሳውን ድርሻ ወስደው ፊት ሁነው በሚመሩ መሪዎች እና የማኅበረሰብ ልሂቃን ነው ብለዋል።

‎ብቃት ያለው መሪ የሚፈጠረው በየጊዜው በሚያገኘው ዕውቀት እና ክህሎት ብቻ ሳይኾን በራሱ ጥረት እና ተነሳሽነት እንደኾነም አንስተዋል።

‎ብቃት ያለው መሪ በየጊዜው ከሚለዋወጠው ዓለማቀፋዊ እና ሀገራዊ ለውጥ ጋር በማጣጣም የአሠራር ባሕሉን፣ ጥንካሬውን፣ ድክመቱን እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ለውጥ የሚሹ ጉዳዮችን በውል ተረድቶ ውጤት ለማስመዝገብ ሌት ከቀን የሚተጋ እና ራዕይ ያለው መኾን ይኖርበታል ነው ያሉት።

‎”ሜሪቶክራሲ” መጽሐፍ ለመሪዎች ግንባታ ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል። መጽሐፉን ለመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ማሳለጫ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል። መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

‎በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) “ሜሪቶክራሲ” ስለ ሰው ብቃት፤ ስለ ዕድል፤ ስለ ጥረት እና ስለ ፍትሐዊ ማኅበረሰብ ለመወያየት የሚጋብዝ መኾኑን ገልጸዋል።

‎መጽሐፉ የሚያስቀምጠው ሃሰብ ነው፤ ሀሳብ ደግሞ ሲነበብ ሰው ሲወያይበት፣ ሲመረመር እና ከተግባር ጋር ሲገናኝ ሕይወት ያገኛል ነው ያሉት። ሜሪቶክራሲ ሰዎች በችሎታቸው፣ በጥረታቸው፣ በብቃታቸው እና በሚያመጡት ውጤት እንዲታዩ የሚያደርግ የአሠራር ጥያቄ መኾኑን አንስተዋል።

‎ሜሪቶክራሲ ችሎታ፣ ጥረት፣ ብቃት እና ውጤት የሚመዘኑበትን ሥርዓት ያነሳል ነው ያሉት፡፡ መጽሐፉ የኢትዮጵያን ርዕዮተ ዓለም ቃኝቷል ብለዋል። ሜሪቶክራሲ ከመደመር እሳቤ ጋር የተያያዘ እንደኾነም አንስተዋል። መደመር አቅምን ይፈጥራል፤ ሜሪቶክራሲ አቅሙን ያሠራል፤ ብልጽግና ውጤቱን ያሳያል ነው ያሉት።

‎ጸሐፊው ከጥንቷ ቻይና የኬጁ” (Keju) የፈተና ሥርዓት፣ ክብሪታንያ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እስከ ሲንጋፖር የኢኮኖሚ ተዓምር ያሉትን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በስፋት የዳሰሰ፣ የምዕራባዊውን እሳቤ ከራሳችን ቀዳሚ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እሳቤ እስከ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ የዕውቀት እና የቢሮክራሲ ጥራት ሙግቶችን በማነጻጸር መዳሰሱንም አንስተዋል።

‎መጽሐፉ ሀገራዊ እና ምሁራዊ ፋይዳው የላቀ መኾኑን ገልጸዋል።

‎ከሁሉም በላይ ይህ መጽሐፍ ለመንግሥት ተቋማት ግንባታ እና ለዘመናዊ ሀገረ-መንግሥት ምስረታ ወሳኝ ኮምፓስ መኾኑንም አንስተዋል።

‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

‎ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleደቅ ደሴት – ታሪኩ፣ ፈንዲሻው እና ማንጎው ሲቃኝ 🥭
Next articleወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከባሕር ዳር ከተማ ጋር!