ደቅ ደሴት – ታሪኩ፣ ፈንዲሻው እና ማንጎው ሲቃኝ 🥭

2

 

ከባሕር ዳር ከተማ በ37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ዳጋ እስጢፋኖስ፣ ናርጋ ስላሴ፣ ቅድስት አርሴማ፣ ኮታ ማርያም፣ ዝባድ ኢየሱስ፣ ጆጋ ዮሐንስ እና ጋደና ጊዮርጊስ በደሴቱ ውስጥ የሚገኙ ገዳማት ናቸው፡፡

🌊 የጣና ሐይቅ በውስጡ ከያዛቸው ታሪክ እና ቅርስ ያቀፉ ደሴቶች መካከል በአቀማመጡ እና በስፋቱ የብዙዎችን ቀልብ የሚስበው ደቅ ደሴት አንዱ ነው። በውኃ የተከበበው ደቅ ደሴት ነፋሻማ አየሩ መንፈስን ያድሳል፤ ሀሳብ እና ጭንቀትን ያርቃል፤ ለዓይን የሚማርከው ተፈጥሯዊ አቀማመጡ ደስታን ይፈጥራል።

ወደ ደቅ ደሴት ለመጓዝ ከጣና ሐይቅ የሚነሳውን ነፋሻማ አየር እየማጉ፤ የሐይቁን የውኃ ጨዋታ እየተመለከቱ፤ በሐይቁ መካከል የሚገኙ ደሴቶችን በርቀት እያስተዋሉ ለሰዓታት የሚፈጅ የጀልባ 🚣‍♀️ ጉዞን መጠቀም ግድ ይላል።

በጣና ሐይቅ ደቅ ደሴት ላይ ተወልዶ ያደገው ዮሴፍ ሽፈራው ደሴቱ በውስጡ ሰባት አድባራት መኖራቸውንም አጫውቶናል።

የአቡነ ሂሩት አምላክ፣ የአጼ በካፋ፣ የአጼ ሱስንዮስ አጽም የሚገኝበት ዳጋ እስጢፋኖስን ጨምሮ ሌሎች ገዳማት እንዳሉም ተናግሯል። የደሴቷን ሀብት በአግባቡ መጠቀም እና ማልማት ከተቻለ የቱሪዝም መዳረሻ በመኾን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻልም ነው የተናገረው።

የደሴቱ ኅብረተሰብ አልባሌ ግጭትና በደልን የሚጸየፉ እና ችግሮችን በውይይት እና በሽምግልና ሥርዓት መፍታትን ባሕል አድርገጎ የሚኖር ነውም ብሏል።

በደሴቱ ሁለት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ደሴቱ በውኃ የተከበበ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ወደ ባሕር ዳር፤ ጎንደር እና ሌሎች አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ጀልባዎችን 🛥 መጠቀም ብቸኛ አማራጩ መኾኑን ነው ያነሳው። ደሴቱ በውኃ የተከበበ በመኾኑ ለዓሳ ምርት ምቹ መኾኑንም ተናግሯል።

ሌላኛው የደሴቷ ነዋሪ ያደለው ረዳት ማኅበረሰቡ በእርሻ ልማት በቆሎ፣ ፈንድሻ፣ በርበሬ እና ዳጉሳን በይበልጥ ያመርታሉ ይላል። ማንጎ እና ሙዝ ደግሞ በቋሚ ተክል በስፋት በማምረት የምግብ ፍጆታቸውን እንደሚሸፍኑም ተናግሯል። በተለይም የደቅ ማንጎ ባሕር ዳር ከተማን የሚመግብ የግንቦት ወር ጸጋ ነው።

የፈንድሻ እና የማንጎ ምርትን በይበልጥ ማልማት ከተቻለ እና የገበያ ትስስር ከተፈጠረ ማኅበረሰቡ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚኾንም አጫውቶናል።

ደቅ ደሴት በሐይቅ ብትከበብም ለእኛ እንደ የብስ ነች ያለው ነዋሪው ደቅ ደሴትን እንደ ጎርጎራ ማልማት ከተቻለ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ መኾን እንደምትችልም አመላክቷል።

#አሚኮ #ደቅ_ደሴት #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የጉበት በሽታን ለመከላከል እና ለመመርመር በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች እየተሠራ ነው” ጤና ሚኒስቴር