“የጉበት በሽታን ለመከላከል እና ለመመርመር በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች እየተሠራ ነው” ጤና ሚኒስቴር

4

 

ዘጠነኛው የአፍሪካ የጉበት በሽታዎች ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ጋስትሮኢንቴሮሎጂ ማኅበር እና የሶሳይቲ ኦፍ ሊቨር ዲዚዝ ኢን አፍሪካ ባዘጋጁት ኮንፈረንስ ከ500 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች እና የፖሊሲ አውጭዎች ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ እየተሳተፉበት ነው።

ይህን ወረርሽኝ ለመግታት አህጉራዊ ተሞክሮዎችን መለዋወጥ፣ ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ መፍጠር እና የተቀናጀ የሕክምና ሥርዓት መዘርጋት የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለጤናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት እና በጉበት ጤና ጥበቃ ላይ እየተከናዎኑ ያሉ ተስፋ ሰጭ ሥራዎች ኢትዮጵያ አሕጉራዊ ኮንፈረንሱን ለማስተናገድ መመረጧን በምክንያትነት ገልጸዋል።

ሀገሪቱ የጉበት በሽታን ከሌሎች ተላላፊ ሕመሞች ጋር በማጣመር በጤና ኤክስቴንሽን እና በመጀመሪያ ጤና ጣቢያዎች ደረጃ ለመከላከል እና ለመመርመር የዘረጋችው የተቀናጀ አሠራር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መልካም ተሞክሮ ኾኗል ብለዋል።

ሌላኛው የተመዘገበው ስኬት ሕጻናት እንደተወለዱ የሚሰጠውን የሄፓታይተስ ቢ ክትባት ማስጀመር መኾኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው ይህም ከ90 በመቶ በላይ ሕጻናትን ከጉበት በሽታ የመከላከል አቅም ፈጥሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጋስትሮኢንቴሮሎጂ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጂግሳ ዳበሳ፣ በአህጉር ደረጃ የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማነስ፣ የቅድመ ምርመራ እና የቫይረስ መጠን መለኪያ መሳርያዎች እጥረት እንዲሁም የመድኃኒቶች ተደራሽ አለመኾን ችግሩን አወሳስቦታል ብለዋል።

በአህጉር ደረጃ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን፣ መመሪያዎችን ለማዘጋጀት፣ እና ቅድመ ምርመራዎችን ወደ ታችኛው የጤና መዋቅር ለማውረድ ኮንፈረንሱ የቅንጅት አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

በኮንፈረንሱ የተሳተፉት ከአሜሪካ የመጡት የጉበት ንቅለ ተከላ ስፔሻሊስት ዶክተር ቅድስት ኪዳኔ በኢትዮጵያ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጉበት ንቅለ ተከላ ማዕከል እየተገነባ መኾኑን ገልጸዋል። የማዕከሉ መገንባት ኢትዮጵያ በዘርፉ እያሳየች ያለችውን ግስጋሴ ያሳያል ብለዋል።

#አሚኮ #ጤና #ኢትዮጵያ 🇪🇹

#አዲስ_አበባ #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ኢብራሂም መሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ምን ተሠራ?
Next articleደቅ ደሴት – ታሪኩ፣ ፈንዲሻው እና ማንጎው ሲቃኝ 🥭