
የሰሜን ሸዋ ዞን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) መሪዎች የታሪክ እና የትውልድ አደራን በማንገብ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን በሁለንተናዊ መልኩ የተሻለ አፈጻጸም እንዲያስመዘግብ የእያንዳንዱ ወረዳ አበርክቶ ከፍተኛ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢኾን የድል ማግስት ስንቅን ሰንቆ ለአዳዲስ ስኬቶች በጋራ መትጋት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በተለያዩ አካባቢዎች የከተሞችን ገጽታ የሚያድሱ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ማከናወን የጥራት መገለጫ እንደነበር ነው የተናገሩት። በሁሉም አካባቢዎች ምርጫን በስኬት ማካሄድ መቻሉ የውጤታማነት ማሳያ ነበር ብለዋል።
እነዚህን መልካም አሠራሮች በሁሉም መመዘኛዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተለይም በመደበኛ የልማት ሥራዎች እና በመንግሥት ልዩ ልዩ ተነሳሽነቶች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የሕዝቡን ጥያቄ እና ፍላጎት በአግባቡ መመለስ እንደሚገባም አሳስበዋል።
እንደ ኮደርስ፣ ዲጂታል መታወቂያ እና የበጋ መስኖ ስንዴ ያሉ ተነሳሽነቶች ውጤታቸው በተግባር እየታየ እንደኾነ ነው የገለጹት። ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ያማከሉ ሥራዎችን በከፍተኛ ደረጃ መፈጸም ለነገ የማይባል ተግባር ስለመኾኑም ተናግረዋል።
በመደበኛ የልማት ዘርፍ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከፍ ለማድረግ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እና የተቋማት ቅንጅት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል።
በቀጣይም ከችግር አዙሪት ወደ መደመር ልዕልና መሻገር የመጨረሻ ግብ በመኾኑ ያልተጠቀምንባቸውን እምቅ አቅሞች ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሐድ መሥራት የሁላችንም ትልቅ ኀላፊነት ነው ብለዋል።
#ደብረ_ብርሃን #መስከረም_07_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
