ሰብልን ከአንበጣ እና ግሪሳ ወፍ እንዴት መከላከል ይቻላል?

4

 

ባሕር ዳር: መስከረም 07/2019 ዓ.ም (አሚኮ) የበረሃ አንበጣ እና የግሪሳ ወፍ በሰብል ምርት ላይ ከባድ ውድመት በማድረስ የምግብ ዋስትና ላይ ሥጋት እንደሚፈጥሩ የዓለም አቀፍ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት መረጃ ያሳያል።

ይህ አደጋ በምሥራቅ አፍሪካ እና የሳህል ቀጠና (Sahel) በተባለው ክልል በሚገኙ ሀገራት ላይ የከፋ ነውም ይላል መረጃው። ይህ ቀጠና ከአትላንቲክ ውቅያኖስ እስከ ቀይ ባሕር ያሉ የምዕራብ እና የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን የሚያጠቃልል ነው።

ኢትዮጵያም በዚሁ ቀጠና የምትጠቃለል ሲኾን በአማራ ክልል ደግሞ በምሥራቁ ክፍል በየጊዜው የበረሃ አንበጣ እና የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ውድመት ያደርሳል።

​✍️የበረሃ አንበጣ፦ አንድ የመንጋ ስብስብ በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 80 ሚሊዮን የሚደርሱ አንበጣዎችን ሊይዝ ይችላል። ይህ ስብስብ በቀን እስከ 35 ሺህ ሰዎች የሚመገቡትን ሰብል ያወድማል።

👉ባሕላዊ የመከላከያ መንገዶች፦

#የብረት እቃዎችን፣ ጣሳዎችን እና ከበሮዎችን በመምታት በሚፈጠር ከፍተኛ ድምጽ መንጋው ሰብል ላይ እንዳያርፍ ማባረር።

#እርጥብ እንጨት እና ቅጠሎችን በማቃጠል በሚፈጠር ጢስ መንጋው እንዳያርፍ ማድረግ ወይም አቅጣጫውን ማስቀየር።

#ገና ክንፍ ያላበቀሉ አንበጣዎችን (Hoppers) ወደተቆፈሩ ጉድጓዶች በመንዳት አፈር መሸፈን ወይም ማቃጠል።

👉ዘመናዊ የመከላከያ መንገዶች፦

#በሰው አልባ አውሮፕላኖች (Drones)፣ በአውሮፕላን እና በተሽከርካሪ ላይ በተገጠሙ መርጫዎች ኬሚካል መርጨት።

#ባዮሎጂካል ተባይ ማጥፊያ፦ “ሜታራይዚየም አክሪደም” የተባለውን ተፈጥሯዊ ፈንገስ በመጠቀም የአካባቢ እና የአፈር ብክለትን ሳይፈጥሩ አንበጣን ማጥፋት።

#የሳተላይት፦ የሰው ሰራሽ አስተተውሎት (AI) እና የመሬት እርጥበትን በመከታተል የአንበጣ መራቢያ ቦታዎችን ቀድሞ መተንበይ እና ማጥቃት።

✍️የግሪሳ ወፍ፦ ይህ የወፍ ዝርያ በተለይ በማሽላ፣ በሩዝ፣ በስንዴ እና በገብስ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ያደርሳል። አንድ የግሪሳ ወፍ በቀን እስከ 10 ግራም እህል ይመገባል።

በዓመት እስከ አራት ጊዜ ድረስ በመራባት እና በአጭር ጊዜ አንድን አካባቢ በመውረር ከፍተኛ ውድመት የማድረስ አቅም አለው።

ምግብ እና ውኃ ፍለጋ እስከ 100 ኪሎ ሜትር ድረስ መጓዝም ይችላል። በፍጥነት መከላከል ካልተቻለ ማሳን ሙሉ በሙሉ የማውደም አቅም አለው።

👉ባሕላዊ የመከላከያ መንገዶች፦

#በመስክ ላይ ቆርቆሮዎችን በማሰር ድምጽ መፍጠር ወይም በወንጭፍ ድንጋይ በመወረወር ወፎቹን ማስበርገግ።

#የሚያብረቀርቁ ቁሳቁሶችን ማሳ ላይ በመትከል ወፎች እንዳይቀርቡ ማድረግ።

#ወፎች ጎጆ በሚሠሩበት እና በሚያርፉበት ዛፍ ላይ እሳት ማጨስ ወይም ጎጆዎቻቸውን በማፍረስ እና የመራቢያ ቦታቸውን ቁጥር መቀነስ።

👉ዘመናዊ የመከላከያ መንገዶች፦

​#ወፎቹ በሚያርፉበት ቦታ ላይ በምሽት በአውሮፕላን ወይም በድሮን ልዩ ወፍ አጥፊ ኬሚካል መርጨት።

#የድምጽ እና የሌዘር ቴክኖሎጂ፦ አዳኝ ወፎችን ድምጽ የሚመስሉ ወይንም የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን እና አረንጓዴ የሌዘር ጨረሮችን በመጠቀም ወፎቹን ከእርሻ ማራቅ።

#ወፎች ሊመገቧቸው የማይችሏቸውን ወይም የመከላከያ እሾሃማ ሽፋን ያላቸውን የሰብል ዝርያዎች ማልማት እንደሚገባ የዓለም አቀፍ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ይመክራል።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ውኃ ውስጥ የተደበቀው እንቁ” በአማራ ክልል
Next article🛺 “የዕለት ጉርሱን ሸጦ ለከተማው ክብር የገዛው የደሴው ብርቱ ወጣት!