
አቶ ባሕሩ ሙሉዓለም በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 10 የደብረ ማርያም አካባቢ ነዋሪ ናቸው። የጣናን ውብ ሐይቅ ዳርቻ መሠረት አድርገው በ300 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የዓሳ ኩሬ በማዘጋጀት ዓሳ የማምረት ሥራቸውን ጀምረዋል። ዓሳ በቀላሉ ሊመረት የሚችል፤ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ፈጣን ተጠቃሚነትን የሚያጎናጸፍ ዘርፍ መኾኑን ይገልጻሉ።
የጫት ማሳቸውን ወደ ዓሳ ልማት መቀየራቸውን የሚናገሩት አቶ ባሕሩ ከ2 ሺህ በላይ ለምግብነት የደረሱ ዓሳዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል። የዓሳ ምርቱን ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረጉ እንደኾነም ገልጸውልናል። በቀጣይ ለሌሎች አርዓያ ለመኾን በሥፋት ለማምረትም አቅደዋል።
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ የዓሳ ግብርና ባለሙያው አበበ ፈንታሁን ክልሉ ለዓሳ ሀብት ልማት ምቹ ጸጋዎች፤ አመቺ የአየር ጸባይ፤ የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ውኃ ሀብት ባለቤት ነው ብለዋል። በክልሉ ጣናን ጨምሮ 10 የተፈጥሮ ሐይቆች፤ 40 ሰው ሠራሽ ግድቦች እና ዋና ዋና ወንዞች ይገኛሉ ነው ያሉት። በጣና እና ተከዜ ወንዝ ጨምሮ በሌሎችም የዓሳ ምርት እንደሚመረት ነው የተናገሩት። ከሀገሪቱ አጠቃላይ ገበያ የዓሳ ምርት ውስጥም ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚኾነው ከዚህ ክልል ይመረታል ብለዋል።
የዓሳ ምርትን ለማዘመን፤ ለማሳደግ እና ዘላቂ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ነው ያሉት። በ2018 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የዓሳ ጫጩት ተባዝቶ ወደ ተለያዩ ውኃማ አካላት ተጨምሯል ብለዋል። 43 ሺህ ቶን ዓሳ ተመርቶም ወደ ገበያ መቅረቡን ነው ያወሱት።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ ስለ መምጣቱም ይልጻሉ። ከዚህ በፊት ዓሳ የሚገኘው በተፈጥሮ ውኃማ አካላት ላይ ብቻ ነበር ያሉት ባለሙያው አሁን ላይ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች እየተመረተ ይገኛል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ሰው ሠራሽ የዓሳ ኩሬ በመገንባት በጓሮ በማምረት የመጠቀም ልምዱ እያደገ መጥቷል ነው ያሉት። በተለይም የዓባይ እና ጣና አካባቢን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የዓሳ የመጠቀም እና የማርባት ልምድ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ባለሙያው እንደ ክልል ከ29 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ መኾናቸውን አንስተዋል።
2019 በጀት ዓመት 52 ሺህ ቶን ዓሳ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ እና ከ2 ሚሊዮን በላይ የዓሳ ጫጩት አባዝቶ ወደተለያዩ ውኃማ አካላት፤ ሰው ሠራሽ ግድቦች እና አርሶ አደሮች የጓሮ ኩሬ ለመጨመር መታቀዱን ነው ያስረዱት። በሁለት ወር ጊዜ ውስጥም ጣናን ጨምሮ ምርት በማይሰጡ ውኃማ አካላት እና በአርሶ አደሮች ኩሬዎች ላይ ከ260 ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩት የመጨመር ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። 2 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ ለገበያ መቅረቡንም ነው የተናገሩት። 3 ሺህ 200 አርሶ አደሮች በጓሮ ኩሬ የአሳ ግብርና ተግባራዊ እንዲያደርጉ መታቀዱንም ገልጸዋል።
ዓሳ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ይገኛል። በ2018 በጀት ዓመት 31 ነጥብ 35 ቶን ዓሳ ወደ ውጭ በመላክ 9 ሺህ 405 ዶላር ገቢ መገኘቱንም አመላክተዋል።
#አሚኮ #የዓሳ_ሀብት #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
