‎የሰላም ጥሪው ፍሬ ማፍራቱን ቀጥሏል !

22
‎‎በምዕራብ ጎንደር ዞን በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የሕዝባቸውን ሰቆቃ ለማስቆም፤ እየደረሰ ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ውድመት ለማስቀረት እና ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ለመውጣት ወስነው ወደ ሰላም አየር ተመልሰዋል።
‎የሰላምን ጥሪ ተቀብለው ወደ ማኅበረሰባቸው ከተቀላቀሉት የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል ወጣት ገበየሁ ዘነበ “ከትግሉ ጀርባ ያለው እውነት የሰው ልጅ ስቃይ እና የግለሰቦች ጥቅም ማስጠበቅ እንደኾነ ስንረዳ ውሳኔያችንን ለመቀየር አልተጠራጠርንም” ይላል። እታገልልሀለሁ የምትለውን እና የወጣህበትን ማኅበረሰብ በሰላም እጦት ረፍት መንሳት ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ነው፤ የሕዝብን ስቃይ በመረዳትም ወደ ሰላም ተመልሼ በልማት ላይ እገኛለሁ” ብሏል ወጣቱ።
‎ሌላኛው ወደ ሰላም አማራጭ የተመለሰው ተቀባ መለሰ “አሁን ትግሉ አቅጣጫውን ስቶ እርስ በርስ መገዳደል፣ መንገድ በመዝጋት እታገልልሀለሁ የምትለውን ሕዝብ ማንገላታት፣ መዝረፍ፣ መግደል እና መቀማት ኾኗል፤ በዚህ መንገድ ከሕዝባችን እና ከሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ጎን ቆመን የሕጻናትን እና የእናቶችን እንባ ማራዘም አልፈለግንም ብሏል። የባዕዳን ተልዕኮ ከሚያስፈጽሙ አካላት ጋር አብሮ የራስን ሕዝብ መበደል አያስፈልግም” በማለትም ድርጊቱን አውግዟል።
‎ባለፉት ጊዜያት ከገንዳ ውኃ አብርሐጅራ፣ ቋራ እና ጎንደር ባሉ መስመሮች በተደጋጋሚ የመንገድ መዘጋት፣ የእገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ ወንጀሎች ሲፈጸሙ መቆየቱን ነዋሪዎቹ አስታውሰዋል።
‎አሁን ላይ በአካባቢው በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍት መኾኑን፣ የእገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ ወንጀልም ከበፊቱ በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል።
‎በምኞት ብቻ ሰላም አይመጣም ያሉት ነዋሪዎቹ በዞኑ ሰላም እንዲሰፍን ታጠቀው ጫካ የገቡ በርካታ ኃይሎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው እንዲገቡ አድርገናል፤ ቀጣይም እንዲገቡ ከታጣቂዎች ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።
‎የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ ደረሰ አዱኛ በዞኑ የተሟላ ሰላም ባለመኖሩ የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተገትቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
‎ይሁን እንጅ በተከናወነው ሕግ የማስከበር ሥራ አሁን ላይ በዞኑ ከበፊቱ የተሻለ አንጻራዊ ሰላም አለ ነው ያሉት።
‎በ2018 በጀት ዓመት ብቻ በዞኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ ኃይሎች እስከ ትጥቃቸው በቡድን የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ወደ ሰላም የመጡትን ወጣቶች መልሶ ማቋቋም መቻሉንም ጠቁመዋል።
‎ፍላጎት ያላቸውንም በተለያዩ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ በማካተት የሰላም ዘብ እንዲኾኑ ማድረግ መቻሉንም መምሪያ ኀላፊው አረጋግጠዋል። የዞኑ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አቶ ደረሰ አዱኛ ተናግረዋል።
‎ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የትምህርት ጥራት እና የትውልድ ግንባታ ቀዳሚ አጀንዳችን ነው” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ