
በአማራ ክልል የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜን ሸዋ ዞን አንዱ ነው። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች በዞኑ በግንባታ ላይ ያሉ እና ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ በትላንትናው ዕለት ጎብኝተዋል።
በሰሜን ሽዋ ዞን ቡልጋ ከተማ አሥተዳደር እና በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙት እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃን በመጠቀም ተኪ ምርትን የሚያመርቱ እና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ናቸው።
አልሚዎች ከክልሉ መንግሥት የሚደረግላቸውን ድጋፍ አድንቀው ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱ ሥራዎቻቸውን አጠናቅቀው በሙሉ አቅም ወደ ምርት እንደሚገቡ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የግንባታ ሥራቸው የተጓተቱ ፋብሪካዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና ማምረት የጀመሩት ደግሞ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ አሳስበዋል።
ለዚህም በሥራ ሂደታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መኾኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ከኢንዱስትሪዎች በተጨማሪ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር እየተገነቡ ያሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ታይተዋል።
#አሚኮ #ኢንዱስትሪ #Ethiopia
#አዲስ_አበባ #መስከረም_05_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አደራው ምንውዬለት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
