“በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተዘጋጅተናል” የደሴ ከተማ ተማሪዎች

3
በደሴ ከተማ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት ዛሬ መስከረም 05 በይፋ ተጀምሯል።
በዕለቱ ለተማሪዎች መልዕክት ያስተላለፉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ሀገር የምትገነባው በትምህርት መኾኑን በመረዳት ተማሪዎች በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ራሳቸውን እንዲያበቁ አሳስበዋል።
ተማሪዎች ስኬታማ ለመኾን ክፍለ ጊዜን በአግባቡ በመከታተል እና ከአልባሌ ቦታዎች በመራቅ ጊዜን በንባብ ማሳለፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። በ2018 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተለይም በመምህር አካለ ወልድ ልዩ ትምህርት ቤት የተመዘገበው አበረታች ውጤት በሌሎች ትምህርት ቤቶችም ተስፋፍቶ እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አደራ ብለዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በከተማዋ በሚገኙ 125 ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመሩን ገልጸዋል።
ለትምህርት ዘመኑ መሳካት የመምህራንን አቅም የማጎልበት እና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።
የተማሪዎች ምገባ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ከማኅበረሰቡ ከተሠበሠበው 7 ሚሊዮን ብር እና ከከተማ አሥተዳደሩ በተመደበው በጀት ከ21 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች እና መምህራን በበኩላቸው በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ኢንዱስትሪዎች ሙሉ አቅማቸውን ይጠቀሙ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article‎በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመማር ማስተማር ሥራ ተጀመረ።