
በሀረሪ ክልል በትምህርት ዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠራ ተገልጿል። በሀረሪ ክልል በትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ አበረታች ስኬቶችን የበለጠ ለማሳደግ እና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ይህንን ያሉት በ2018 የትምህርት ዘመን በዘርፉ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ባለድርሻ አካላት የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት በተሰጠበት መርሐ ግብር ላይ ነው። በንግግራቸውም መንግሥት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እና የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መቅረጽን አንገብጋቢ አጀንዳ አድርጎ እየሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
በክልሉ በዘርፉ በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ለዚህም የ2018 የትምህርት ዘመን ብሔራዊ ፈተና ውጤት ማሳያ መኾኑን ተናግረዋል።
አሁንም ለትምህርት የደረሱ ታዳጊዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት ቤት በማስገባት፣ የተማሪዎችን ውጤት፣ ሥነ-ምግባር እና ክህሎት የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትምህርት ውጤታማነት በመንግሥት ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ ባለመኾኑ የወላጆች፣ የመምህራን እና የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ በመጠቆም ሽልማት የተበረከተላቸው አካላትም ለላቀ ውጤት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል እና የተማሪዎችን ውጤት የማሳደግ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አክለውም በ”ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ በ2018 የትምህርት ዘመን ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት መሠብሠብ መቻሉን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በዘርፉ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የዕውቅና እና ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
