
በአማራ ክልል በ2018/19 የምርት ዘመን የተያዘውን የምርት ግብ ለማሳካት የአረም እና የተባይ ቁጥጥር ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ እና በምሥራቁ የክልሉ አካባቢዎች የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የሚያስችል የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከ5 ሚሊዮን 589 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በክረምቱ መግቢያ ወቅት በምሥራቁ የክልሉ ክፍል የዝናብ መዘግየት የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ በሁሉም አካባቢዎች በቂ እና ተመጣጣኝ ዝናብ በመኖሩ ሰብሉ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ቁመና ላይ ይገኛል።
የታቀደውን ምርት ለማሳካት አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ከአረም እና ተባይ ነፃ ማድረግ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ በአረም ምክንያት ብቻ እስከ 12 በመቶ የሚደርስ ምርት ሊባክን እንደሚችል ጠቁመዋል።
በመሆኑም አርሶ አደሮች ማሳቸውን በየጊዜው በመፈተሽ፣ ባሕላዊ እና ዘመናዊ የተቀናጀ የተባይ መከላከያ ዘዴዎችን እና የፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን በወቅቱ እና በሥርዓቱ መጠቀም እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ከነሐሴ 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች የግሪሳ ወፍ ወረርሽኝ መከሰቱን ዶክተር ማንደፍሮ አረጋግጠዋል።
ችግሩን በአፋጣኝ ለመከላከል ለፌዴራል መንግሥት ጥቆማ መደረጉን ገልጸዋል። ወረርሽኙን በአውሮፕላን ኬሚካል በመርጨት ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ወደ አካባቢው እየተጓጓዙ መኾኑን እና ሰብል ላይ ጉዳት ሳይደርስ ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ባሕር ዳር #መስከረም_04/2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
