
በኢትዮጵያ የእንሰሳት ሃብት ከቁሳዊ ሃብትነት ባለፈ የማኅበራዊ መስተጋብር፣ የባሕል እና የኑሮ መሠረት ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል። ማኅበረሰቡ ከትናንት እስከ ዛሬ ከእንሰሳት ሃብቱ ጋር ያለው ቁርኝት እጅግ ከፍተኛ ነው። የቁም እንሰሳትን በስፋት ማራባት የአርሶ አደሮች የኢኮኖሚ አቅም መለኪያ እና የክብር መገለጫ ተደርጎ ይቆጠራል።
ከዚህ በተጨማሪም ከዕለት ምግብ ፍጆታ፣ ከወተት፣ ከሥጋ እና ከቅቤ አቅርቦት ባለፈ የገጠሩ የግብርና ሥራ በእንስሳት ጉልበት ላይ የተመሠረተ በመኾኑ እንሰሳት ለማኅበረሰቡ የሕልውና ያህል ትልቅ ትርጉም አላቸው።
ኾኖም የእርባታ ሥርዓቱ እና አጠቃቀሙ ከባሕላዊ እና ልማዳዊ አሠራር ያልዘለለ ነበር። ምርታማነትን ከማሳደግ እና ጥራትን ከማስቀደም ይልቅ በእንሰሳት መንጋ ጋጥ መሙላት ላይ ብቻ ያተኮረ አስተሳሰብ የነገሠበት ስለነበር ሕዝቡም ኾነ በየዘመናቱ የነበሩ መንግሥታት ሃብቱን በሚገባ ተጠቅመውበታል ማለት አይቻልም።
ይህም ሕዝቡ ከጸጋው እኩል እንዳይበለጽግ፤ ሀገርም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓት ቆይቷል። በዘርፉ ከቁጥር ይልቅ ለእሴት እና ጥራት ትኩረት አለመሰጠቱ፤ የእንሰሳት ተዋጽኦ ምርቱ በቴክኖሎጂ እና በሳይንሳዊ መንገድ አለመደገፉ፤ አርሶ አደሮች የእንሰሳት ሃብታቸውን ወደ ተደራጀ የገበያ ሥርዓት አለማስገባታቸው እና ሃብቱን ከባሕላዊ አሠራር አስወጥቶ ክልላዊ እና ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን መምራት ወደሚችልበት ደረጃ እንዲሸጋገር አለመደረጉ ሀገርን በእጅጉ ጎድቷት ቆይቷል።
አሁን ከዘመናት አለማስተዋል በኋላ ትኩረት አግኝቷል። እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል ለዘመናት የዘለቀውን ባሕላዊ አሠራር በመቀየር አዳዲስ የለውጥ ሥራዎች ተጀምረዋል። ልክ እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ የእንሰሳት ሃብት ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ ተደርጎም ተወስዷል። በዚህም የወተት ላም፣ የዶሮ እና መሰል እንሰሳትን ዝርያ በማሻሻል፤ ዘመናዊ የመኖ አቅርቦት እና የእንሰሳት ጤና አጠባበቅ ሥርዓቶችን በመተግበር ዘርፉን ለማዘመን ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የአማራ ክልል እንሰሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) እንደሚሉት ቀደም ባሉት ጊዜያት የእንሰሳት ሃብት በገጠር እና ባልተማረ ሰው ብቻ የሚሠራ ተደርጎ ይታይ ነበር። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ያንን እሳቤ የሰበረ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ይጠቅሳሉ። በአሁኑ ወቅት የተማረው የሰው ኀይል ወደ ዘርፉ በሰፊው እየገባበት እና በከተሞችም ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ እየተተገበረ በመኾኑ ዘርፉ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል ነው ያሉት።
እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ ዘርፉን ለማዘመን ወደ ሥራ ሲገባ የምግብ ሥርዓትን በማሻሻል ከተረጅነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ፣ ተኪ ምርት እና የወጭ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሬን የማስቀረት ግቦች ተቀምጠው ነው።
ከዚህ አኳያ ሲታይ በሁሉም ረገድ በተገኙት ተጨባጭ የኾኑ እና የማኅበረሰቡን ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች የእንሰሳት ሀብት ተኪ የሌለው ዘርፍ መኾኑ በተግባር ተረጋግጧል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ዘርፉን ወደተሟላ ዘመናዊ አሠራር የማሸጋገር ሥራው አሁንም ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ይላሉ። በየአንዳንዱ አካባቢ ያለውን ጸጋ እና አቅም አሟጥጦ በመጠቀም የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዚህም በ2019 በጀት ዓመት በማክሮ ደረጃ ትልቅ ዕቅድ ተይዟል። ዘርፉን ወደ ዘመናዊ አሠራር የማሸጋገር እና ዘላቂነቱን የማረጋገጥ ሥራ በማከናወን፣ የእንሰሳት ልማቱ ለክልሉ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አማራጭ እንዲኾን በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
